Fana: At a Speed of Life!

የህወሓት አጥፊ ቡድን በራሱ ወገን ላይ የፈፀመው ተግባር የሚያሳፍር፣ አሳዛኝና ታይቶ የማይታወቅ ነው- የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህወሓት አጥፊ ቡድን በራሱ ወገን ላይ የፈፀመው ተግባር የሚያሳፍር፣ አሳዛኝና ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር አብዱራሃማን አል ዶሰሪ ገለፀጹ።

በኳታር የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ ከኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር፣ ተቀማጭነታቸው በዶሃ ከሆኑ የኤርትራ፣ የሶማሊያ፣ የኬንያ እና የሱዳን አምባሳደሮች እንዲሁም በዶሃ የሴት አምባሳደሮች ቡድን ማለትም ለአሜሪካ፣ የሜክሲኮ፣ የታንዛኒያ፣ የግሪክ፣ የኒዘርላንድ፣ የካናዳ እና ስፔን አምባሳደሮች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም በዶሃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሳይንስ፣ የትምህርት እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) እና የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) ተወካዮች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ገለፃ ማድረጋቸውን በኳታር የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

በውይይቶቹም አምባሳደር ሳሚያ የህወሓት አጥፊ ቡድን በሀገር የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ አሳፋሪ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እና አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ እየወሰደ ያለውን ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ በተመለከተ ገለጻ በመስጠት ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር አብዱራሃማን አል ዶሰሪ በዚሁ ወቅት፥ የኳታር መንግስት ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን አስታውቀዋል።

የህወሓት አጥፊ ቡድን በራሱ ወገን ላይ የወሰደው እርምጃ “የሚያሳፍር፣ አሳዛኝ እና ታይቶ የማይታወቅ” ክስተት መሆኑን አንስተዋል።

አምባሳደሮቹ እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮቹም በበኩላቸው የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን ድርጊትን ማውገዛቸው ኤምባሲው አስታውቋል።

መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ተገቢ እና ከአንድ ሀገር መንግስት የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.