Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን በ23 የጸረ-ሠላም ኃይሎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የጁንታውን የሕወሓት የጥፋት ተልዕኮ ይዘው በንጹኃን ዜጎች ላይ ጥቃት ሲያደርሱ በነበሩ 23 የጸረ-ሠላም ኃይሎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የዞኑ ኮማንድ ፖስት አስታውቋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ የጸጥታ አካላት ትናንት በወሰዱት የተቀናጀ እርምጃ በዞኑ ማንዱራ ወረዳ 17 ፣ በዳንጉር ወረዳ 2፣ በጉባ ወረዳ ደግሞ 4 በድምሩ 23 የጸረ-ሠላም ኃይሎች መደምሰሳቸውን ኮማንድ ፖስቱ ገልጿል፡፡
ኮማንድ ፖስቱ በመተከል ዞን የጁንታውን የህወሓት የጥፋት ተልዕኮ በመያዝ በተለያዩ አካባቢዎች በንጹኃን ዜጎች ላይ ጥቃት እያደረሠ ባለው የጸረ-ሠላም ኃይል ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ከወትሮው በተለየ መልኩ አጠናክሮ መቀጠሉንም አመልክቷል፡፡
እነዚህ ጸረ-ሠላም ኃይሎች የመጥፊያ ጊዜያቸው መቃረቡን ተከትሎ አሁንም ቢሆን በማህበረሰቡ ላይ ጥቃት ከማድረስ የማይቆጠቡ መሆኑን ገልጿል።
በመሆኑም ህዝቡ በተደራጀ አግባብ አካባቢውን ከፀረ-ሠላም ሃይሎች ከመጠበቅ ባሻገር ከፀጥታ ኃይሉ ጎን ሆኖ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ እና የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ተግባር እንዲደግፍም የዞኑ ኮማንድ ፓስት ጥሪ ማቅረቡን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈትቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.