Fana: At a Speed of Life!

ገለልተኛ ብሔራዊ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት ሊቋቋም ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ገለልተኛ ብሔራዊ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት ሊቋቋም መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

መንግስት የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራሙን በስኬት ለማስፈፀምና ጥራት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ የባለሙያዎችን ምክር እንዲሁም ምክረ ሀሳብ መቀበል ጠቃሚ ነው ብሎ እንደሚያምንም ተገልጿል።

ገለልተኛ ከሆኑ ምሁራንና ባለሙያዎች ሀሳብ መቀበል የፖሊሱ አካታችነትን ይጨምራል፣ ሀገሪቱ ያለችበትን ውስብስብ የሆነ ደህነትና የተያያዙ ማህበራዊ ችግሮችን ለመረዳት፣ ዘርፈ ብዙ የፖሊሲ አማራጮችን ለመመርመር እና መፍትሄ ሀሳቦችን ለማመንጨት እንደሚያስችልም ተገልጿል።

እንዲሁም የመንግስት ፖሊሲዎች በህዝብና በተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በኩል ያላቸውን ተቀባይነት እንዲጨምር ያግዛል ነው የተባለው።

በመሆኑም መንግስት ገለልተኛ ብሔራዊ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት ለማቋቋም መወሰኑን ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መረጃ ያመለከተው።

ምክር ቤቱ ገለልተኝነቱን ጠብቆ በነፃነት የሚሰራ ሲሆን፥ ከመንግስት ጋር በየጊዜው የሚመክር መሆኑን ታውቋል።

የምክር ቤቱ አባላት በቁጥር 15 እንደሚሆኑ የሚጠበቅ ሲሆን፥ አባላቱም በሙያቸው
የተካኑና የተመሰገኑ፣ በዘርፉ ተካበተ የስራ ልምድ ያላቸው፣ ሀገርን የማገልገል መንፈስ ያላቸው፣ በስራ ዘርፍ፣ በጾታ እና በሌሎች ገጽታዎች ብዝሃነት ያላቸው፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚም ሆነ ማህበራዊ እውነታን ጠለቅ ብለው የተረዱ፣ የሀሳብ ልዩነትን በመረጃ እና በሀሳብ ውይይት በመፍታት የጋራ መፍትሄ የመሻት ክህሎት ያላቸው እና ከሁሉም በላይ ለሀገራቸው ፍቅር እና ተቆርቋሪነት እንዲሁም የአገልጋይነት መንፈስ የሚሰማቸው ሊሆኑ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

ለዚህም እጩ አባላትን ለመቀበል ጥሪ የወጣ ሲሆን፥ አባላቱን የመለየት ሂደት ግልጽ እና አሳታፊ እንዲሆን መንግስት በይፋ የእጩ አባላትን ጥቆማ ለመቀበል መወሰኑን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

በመሆኑም ገለልተኛ ብሔራዊ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት አባል ለመሆን ፍላጎት እና አቅም ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራን የግል ማህደራቸውን በ15 ቀናት ውስጥ policyunit@pmo@gov.et የኢሜይል አድራሻ እንዲልኩም ጥሪ አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.