Fana: At a Speed of Life!

መንግስት በትግራይ በጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ ውስጥ የሶስተኛ ወገን ተሳትፎ አያስፈልግም – አምባሳደር መለሰ አለም

አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በኬንያ የኢፌዴሪ አምባሳደር መለሰ አለም “የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል በጀመረው የህግ ማስከበር ዘመቻ ውስጥ የሶስተኛ ወገን ተሳትፎ አያስፈልግም” ሲሉ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ መንግስት በውስጥ ጉዳዩ ላይ የሌሎች ሀገራት ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልገው ገልፀው፤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ቡድኑን እየወጋች ነው የሚለውን ሀሳብ አጣጥለዋል።

ኢትዮጵያ የሌላ ሀገራት ድጋፍ ሳይታከልበት በመከላከያ ሰራዊቷ የውስጥ ጉዳይን መፍታት እንደምትችልም ገልጸዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ሆነ በመላው አፍሪካ ሰላም እና ጸጥታን በማስፈን ታላቅ ስም ያለው ሰራዊት ነው ብለዋል።

መንግስት የህግ ማስከበር ዘመቻውን በትግራይ የጀመረበትን ሁኔታ ሲገልጹ፤ ጁንታው የህወሓት ቡድን ከ20 ዓመታት በላይ ክልሉን ሲጠብቅ፤ ህዝብን በልማት ሲያገለግል በነበረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት ማድረሱን ጠቁመዋል።

የህወሓት ቡድን ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት ህግን በጣሰ መልኩ ሀገር የማተራመሱን ስራ ሲሰራ መንግስት ከመጠን በላይ መታገሱንም ነው የተናገሩት።

ቡድኑ የመንግስትን ትዕግስት እንደ ድክመት በመቁጠር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች ለመቀበል ዝግጁ እንዳልነበረ ገልጸዋል።

ባለፉት 27 በዓመታት ሀገሪቱን ሲመራ የነበረው የህወሓት ቡድን የመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ፤ ከሌሎች የታጠቁ ቡድኖች ጋር በመሆን የሀገሪቱን ጸጥታ ሲያውክ እንደነበርም አንስተዋል።

መንግስት ሀገራዊ ምርጫው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክስተት ምክንያት እንዲራዘም ቢያደርግም ቡድኑ ይህን ባለመቀበል ህገወጥ ምርጫ ማካሄዱን አስታውሰዋል።

የቡድኑን የሴራ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ መንግስት በትግራይ ክልል የጀመረው የህግ ማስከበር ስራ የህገ መንግስት የበላይነትን ማረጋገጥ እና የትግራይን ዜጎች ከጁንታው ነጻ ለማውጣት ያለመ ነውም ብለዋል አምባሳደር መለስ።

አምባሳደር መለሰ አለም ህወሓት ያሰማራቸው ታማኝ የልዩ ሀይል እና ሚሊሻ አባላቱ በማይካድራ በንጹሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ ስለመፈጸማቸውም ጠቁመዋል።

ይህን አሰቃቂ የንጹሃን ግድያ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጭምር ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

በግጭቱ አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ሱዳን ለተሰደዱ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ እና መልሶ ለማቋቋም የባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ኮሚቴ ወደ ስራ መግባቱን ነው የገለፁት።

በትግራይ የተጀመረው የህግ ማስከበር ዘመቻ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት አምባሳደሩ አላማውም ጁንታውን የህወሓት ቡድን ለህግ የማቅረብ ተግባር እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ የኬንያውን ኬቲኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጠቅሶ ዘግቧል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.