የሀገር ውስጥ ዜና

በሰሜን ሸዋ ዞን 469 የኦነግ ሸኔ አባላት፣ የቡድኑ ተላላኪዎች እና ሽፍቶች በቁጥጥር ስር ዋሉ

By Tibebu Kebede

November 27, 2020

አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን 469 የኦነግ ሸኔ አባላት፣ የቡድኑ ተላላኪዎች እና ሽፍቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ፡፡

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ታሪኩ ድሪባ እንደገለጹት ነዋሪው በኦነግ ሸኔ አባላትና ሽፍቶች ሰላሙን ሲያጣ ቆይቷል፡፡

በዞን 415 የኦነግ ሸኔ ተላላኪዎች እና 47 ሽፍቶች በቁጥጥር ስር ሲውሉ 7 የኦነግ ሸኔ አባላት ደግሞ ተማርከዋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኦነግ ሸኔ አባላትና ሽፍቶች በተጨማሪ፣ 12 የኦነግ ሸኔ አባላት እና 8 ሽፍቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡

ወንጀል ሲፈፀምባቸው የነበሩ ከ100 በላይ የጦር መሳሪያ እና 27 ሺህ የተለያዩ የጥይት አይነቶች ተይዘዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ እንደሻው ብርሃኑ ለኦቢኤን እንደተናገሩት ህዝቡ ልማት፣ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደርና ሰላም ይፈልጋል፡፡

ስለዚህም የፀረ-ሰላም ኃይሎችን ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን እያጋለጠ ይገኛል ብለዋል፡፡

በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡