Fana: At a Speed of Life!

ተቋሙ አዲስ የቆጣሪ ማንበቢያ ዘመናዊ መሳሪያ በስራ ላይ አዋለ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 18 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቆጣሪ ማንበቢያ መሣሪያ ስራ ላይ ማዋሉን አስታወቀ፡፡

አዲሱ የቆጣሪ ማንበቢያ መሳሪያ ኮመን ሜትር ሪዲንግ ኢንስትሩመንት /CMRI/ የተሰኘ በእጅ የሚያዝ ዘመናዊ መሳሪያ ነው ተብሏል።

የቆጣሪ አንባቢው በእያንዳንዱ የድህረ ክፍያ የቆጣሪ ተጠቃሚ ደንበኛ አካባቢ ሄዶ እንዲያነብ የሚያስገድድ ሲሆን ይህም ከኤሌክትሪክ የፍጆታ ሂሳብ ንባብ ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመቀነስ ያስችላል ነው የተባለው፡፡

መሳሪያው በ50 ሜትር ወይም ከዛ ባነሰ ርቀት ላይ በመሆን የደንበኛ ተከታታይ ቁጥር በማስገባት የቆጣሪ ንባብ መውሰድ የሚያስችል ሲሆን፤ የተቀዳውን ንባብ ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን ለማረጋገጥም ለአንባቢው እድል የሚሰጥ ነው፡፡

መሳሪያው የንባብ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ የአሰራር ሂደቶችን ለማፋጠን፣ የጊዜና የሃብት አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ በወረቀት ላይ የተመሰረተ አሰራር ስርዓትን ለማስቀረት፣ የንባብ ምዝገባ ስህተቶችን ለማስወገድ፣ የደንበኞችን ቅሬታን ለመቀነስ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ያስችላል ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ደንበኞች ሂሳባቸውን በወቅቱ እንዲከፍሉ እና ተቋሙ ገቢን በብቃት ለመሰብሰብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑንም አስታውቋል፡፡

2 ሺህ በእጅ የሚያዙ የቆጣሪ ማንበቢያ መሳሪዎችን ከ400 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ገዝቶ በከተማ አስተዳደሮችና በክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮዎች በማሰራጨት የንባብ አሠራር ሂደቱን ከወረቀት ስራ ወደ ዲጂታል አሰራር እየቀየረ ይገኛል፡፡

ቆጣሪ ማንበቢያው እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በሁሉም ማዕከላት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ይሆናል ነው የተባለው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.