ዶናልድ ትራምፕ የፔንሲልቫኒያው የጆ ባይደን ውጤት እንዲታገድ ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ ሆነ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጆ ባይደን በፔንሲልቫኒያ ያስመዘገቡት ውጤት ይታገድልኝ ሲሉ ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ ሆነ፡፡
የአሜሪካ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ትራምፕ በግዛቲቱ የባይደን አሸናፊነት ውድቅ ይደረግ ዘንድ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አድርጎታል፡፡
ትራምፕ በደፈናው ምርጫው ተጭበርብሯል የሚል ውንጀላ አቅርበዋል፤ ከዚህ ጋር ተያይዞም በግዛቲቱ በፖስታና በኢሜል የተሰጡ ድምጾች ውጤት ውድቅ ይደረግልኝ ብለዋል፡፡
ሌሊቱን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ደግሞ “በምርጫው ባይደን ብዙ የተጭበረበሩ ድምጾችን አግኝተዋል” በሚል ውጤቱ እንዳልተዋጠላቸው አስታውቀዋል፡፡
አያይዘውም “ጆ ባይደን ያገኟቸው ድምጾች ያልተጭበረበሩና ህጋዊ መሆናቸውን ሲያረጋግጡ ብቻ ነጩ ቤተ መንግስት ይገባሉ” ሲሉም በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ችሎቱን የመሩት ሶስት ዳኞች የትራምፕ ቡድን ድምጽ ተጭበርብሯል በሚል በቂ ማስረጃ እንዳላቀረበ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የባይደን ውጤት ይታገድልኝ ለሚለው ጥያቄ ጥሩ የሚባሉ አሳማኝ ነጥቦችን አላነሳምም ነው ያሉት፡፡
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ትራምፕ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ለመቀልበስ ባደረጉት ሙከራ የገጠማቸው ሌላ ሽንፈት ነው ተብሏል፡፡
ትራምፕ በትናንትናው እለት ጆ ባይደን በኤሌክቶራል ኮሌጁ አሸናፊ መሆናቸው ከታወጀ ስልጣን ሊለቁ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተው ነበር፡፡
ምንጭ፦ ቢቢሲ