Fana: At a Speed of Life!

ህዝቦች በአንድነት፣ በመተሳሰብና በወንድማማችነት እንዳይኖሩ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ የቆየው የጁንታው ቡድን ላይመለስ ፈራርሷል፡- ብልፅግና ፓርቲ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረ ብሄራዊ አንድነት ሁሌም ያሸንፋል ሲል የብልፅግና ፓርቲ ፓርቲ አስታወቀ።

የብልፅግና ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫው በሀገሪቱ ባለፉት ሁለት አመታት ተኩል የህዝቡን እውነተኛ የዴሞክራሲ ጥያቄ ለመመለስ እና ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው የመንግስት ስርዓት ለመገንባት ተጨባጭ ለውጥ በማስፈለጉ በህዝብ ግፊት የተቀጣጠለውና በፓርቲው ሳቢነት እውን የሆነው የለውጥ ሂደት ለኢትዮጵያዊያን ብሩህ ተስፋን ፈንጥቋል ብሏል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ ያወጣው ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።

የህወሓት ጸረ ህዝብ አጥፊ ቡድን ኢትዮጵያውያን የራሳቸው ያደረጉትን ለውጥ ለማደናቀፍና ሀገርን ለመበታተን ያልሞከረው የጥፋት መንገድ አልነበረም ነው ያለው፡፡

ይህ ህገወጥ ቡድን በሀገሪቱ ጠንካራ ህብረብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንዳይሳካ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለእኩይ ተግባሩ ማስፈጸሚያ የሚሆኑ አካላትን በማደራጀትና በማስታጠቅ የዜጎች መፈናቀል፣ ግድያ፣ የንብረት ውድመት፣ እና ሌሎችም የሀገሪቱን ሰላምና ጸጥታ የሚያናጉ በርካታ ተግባራትን በመፈጸም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷልም ሲል አስታውሷል፡፡

በተለይም በአገሪቱ የለውጥ አመራሩ ኃላፊነት ከተረከበ በኋላ ጁንታዉ ራሱን ከፌዴራል ስርዓቱ ነጥሎ መቐለ ከተማ ከመሸገ በኋላ በአንድ በኩል ለጦርነት እየተዘጋጀ በሌላ በኩል በፌዴራል መንግስት የሚወጡ ህጎችን፣ የሚሰጡ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎችን ባለመፈፀም በፌደራል መንግስቱ ላይ አፍራሽ መግለጫዎችን እስከማውጣት የደረሰ ተግባር ሲፈጽም ቆይቷል ብሏል፡፡

መግለጫው የህወሓት ቡድን የሀገሪቱ ህዝቦች ያነሷቸውን የልማት፣ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በወንድማማችነት እና በአንድነት መንፈስ ማረጋገጥ እንዲቻል በሀገራዊ ለውጡ እንዲካተት ባለፉት ሁለት አመታት ተኩል በርካታ ተደጋጋሚ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም ሁሉንም የሰላም ጥሪዎች እየረገጠ የጦርነት ነጋሪት ሲጎስም ቆይቶ የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት የሆነውን ህብረብሄራዊ የሀገር መከላከያ ስራዊት ከጅርባው በመውጋት የእናት ጡት ነካሽ ከሃዲ ቡድን መሆኑን አረጋግጧል ሲል ያነሳል፡፡

አይደለም በአንድ ሀገር ልጆች ላይ በጠላት ሀገርም ላይ ተደርጎም በማይታወቅ መልኩ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችና አባላት በማንነታቸው በመለየት ፍጹም ባልገመቱበት ሁኔታና ጊዜ በበርካታ የሰሜን ዕዝ ካምፖች የተቀናጀ ጥቃት በመሰንዘር ውድ ሰራዊት አባላት ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድል፣ ትጥቆች እንዲዘረፉ እና እንዲወድሙ አድርጓል፡፡

በማይካድራ ከተማ ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ ዜጎችን አስቀድሞ በማንነታቸዉ በመለየት ከ700 በላይ ንጽሃን ለፍቶ አዳሪ ዜጎች ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲጠፋ በማድረግ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደፈፀመም ነው በመግለጫው ያብራራው፡፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ይህንን ገደብ ያለፈ ጥቃትና የውንብድና ተግባር ለመመከትና የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስቀጠል የህግ ማስከበር እርምጃ ሲወስድ ቆይቶ የትግራይ ክልልን ከጁንታው አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ነጻ አድርጓል፡፡

ሰራዊቱ በተቀዳጀው ድል መላው የሀገሪቱ ህዝቦች እንኳን ደስ አላችሁ ያለው ፓርቲው በተለይም በጁንታው አገዛዝ ስር ከፍተኛ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጽእኖ ስር ለነበረው የትግራይ ህዝብ እንኳን ለዚህች ታሪካዊ ቀን አበቃችሁ ለማለት እንወዳለን በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ባልተጠበቀ ሁኔታ የህወሓት ጁንታ ቡድን ከጀርባ ጥቃት  ቢሰነዝርባችሁም ራሳችሁን በፍጥነት እንደገና በማደራጀት ራስን ከመከላከል አልፋችሁ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስከበር ለከፈላችሁት መስዋዕትነትና ላሳያችሁት ጀግንነት ታላቅ ምስጋና እያቀረብን ሀገሪቱ ከዚህ ከሃዲና አረመኔ ቡድን በማጽዳት ቀና ብለን እንድንራመድ ስላደረጋችሁን የተሰማንን ሀገራዊ ክብር ስንገልጽላችሁ በታላቅ ኩራት ነውም ብሏል፡፡

የሀገሪቱ ህዝቦች በአንድነት፣ በመተሳሰብና በወንድማማችነት እንዳይኖሩ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ የቆየው የጁንታው ቡድን ላይመለስ ፈራርሷል፡፡

በመሆኑም ህብረ ብሄራዊትና የመተሳሰብና የአንድነት ምልክት የሆነች ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም በጁንታዉ የአገዛዝ ጫና ሥር የነበረው የትግራይ ህዝብ ግምባር ቀደም ተሳታፊና ተጠቃሚ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡

የወንጀለኛዉን ጁንታ አባላት ከተደበቁበት አድኖ ለፍርድ ከማቅረብ ጎን ለጎን በህግ ማስከበር እርምጃው ሂደት ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አገራቸዉ ተመልሰዉ እንዲቋቋሙና እብሪተኛው ጁንታ ያፈራረሳቸው የህዝብ መሰረተ ልማቶች በፍጥነት ተጠግነው ለአገልግሎት እንዲውሉ በልዩ ትኩረት የሚሰራ ይሆናል፡፡

የፓርቲው አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና መላዉ የኢትዮጵያ ህዝቦች በትግራይ ክልል የህዝብ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ የእለት ደራሽ ሰብዓዊ አገልግሎቶች በፍጥነት ደርሰዉ እንዲሰራጩና ህብረተሰቡ ወደ መደበኛ የእለት ተእለት ህይወቱ እንዲመለስ በሚደረገዉ ርብርብ ውስጥ አስተዋፅኦ እንዲያበርክቱ ጥሪ አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.