Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን መደገፍ የሚያስችል የ16 ሚሊየን ብር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 21፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም የዕለት ወጫቸውን መሸፈን ለማይችሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ለመደገፍ የሚያስችል የ16 ሚሊየን ብር ፕሮጀክት ይፋ ማድረጉን አስታወቀ።

ፕሮጀክቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት ነው በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው።

ለአንድ አመት የሚቆየው ይኸው ፕሮጀክት በ45ቱም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የእለት ወጪያቸውን መሸፈን ለማይችሉ 4ሺህ ተማሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።

ኩባንያው ገቢ የሚሰበስበው የሀገሪቱን የልማት ውጥኖች ከግብ ለማድረስና የህብረተሰባችንን መሰረታዊ ችግሮች በመለየት ለመፍታት እንደሆነም ሥራ አስፈጻሚዋ ገልፀዋል፡፡

በዚህም ፕሮጀክት ቅድሚያ ከተሰጣቸው የህብረተሰብ ችግሮች መካከል የትምህርት ዘርፉን መደገፍ  አንዱና ዋነኛው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው ለተማሪዎች የወደፊት ራዕያቸው እንዲሳካ እያደረገ ያለው የድጋፍ ጥረት ተማሪዎችን ከማገዙም በላይ ዩኒቨርስቲዎችን ለተሻለ ሥራ የሚያነሳሳ ተግባር መሆኑ ተመላክቷል።

ኢትዮ-ቴሌኮም እንዲህ ዓይነቱን ድጋፍ ማድረግ የጀመረው በ2011ዓ.ም በ13 ዩኒቨርሲቲዎች ለሚማሩ 853 ተማሪዎች እንደነበረም ተገልጿል።

ኢትዮ ቴሌኮም  ከ2006 ዓ.ም ጀምሮም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ተማሪዎችን ጨምሮ፣አረጋውያን፣ ችግረኛ ቤተሰቦችን ፣አካል ጉዳተኞችን እና ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የሙያ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.