የተቀናጀ የሎጅስቲክስ አገልግሎት መቅረቡ ለሰራዊቱ ድል የላቀ ሚና ነበረው – ሜ/ጄ አብዱራህማን እስማኤል
አዲስ አበባ፣ ህዳር 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህብረት ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጄነራል አብዱራህማን እስማኤል የተቀላጠፈና የተቀናጀ የሎጀስቲክስ አገልግሎት መሰጠቱ ሰራዊቱ ጁንታውን ከስራ ውጭ እንዲያደርግ የላቀ ሚና እንደነበረው ተናገሩ፡፡
ከሃዲው የህውሓት ቡድን ባልተጠበቀ ሁኔታ በሰራዊቱ ላይ ጥቃትና ዝርፊያ መፈፀሙን ተከትሎ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ህግ ለማስከበር ለተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት የተቀናጀና ውጤታማ የውጊያ ድጋፍ አገልግሎት እየተደረገ መሆኑን ሜጀር ጄነራል አብዱራህማን ገልጸዋል፡፡
ከሀዲው ለረጅም ጊዜ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱንና በአካባቢው ተሰማርቶ ለሚገኘው ሰራዊትም የሎጀስቲክስ አገልግሎትና ወታደራዊ ድጋፍ እንዳያገኝ የተለያዩ መሰናክሎችን ለመፍጠር መሞከሩን አስታውሰዋል፡፡
ሆኖም ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ወታደሮችን ወደ ግዳጅ ቀጣና ለማሰማራትና በግዳጅም ላይ አስፈላጊውን የውጊያ ንብረቶችን በጊዜው ለማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በውጊያው የተንጠባጠቡ የጠላት ንብረቶችን በመሰብሰብና ጥገና የሚያስፈልጋቸውንም በቦታው ጥገና እየተደረገ መሆኑን ያወሱት አዛዡ በእልህና በጀግንነት በመሰራቱ ሴራውን በማክሸፍ በአጭር ጊዜ ድልን ለመቀዳጀት አስችሎናል ነው ያሉት፡፡
በሰራዊቱ ላይ የተፈፀመውን ክህደት ተከትሎ መላው ህዝብ ለሰራዊቱ እያደረገ የሚገኘው ድጋፍ ለወታደሩ ከፍተኛ ሞራል በሎጀስቲኩም ደግሞ ትልቅ አቅም እንደሆነ መናገራቸውን ከመከላከያ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡