Fana: At a Speed of Life!

የሐረሪ ክልል ከጸረ ሰላም ሀይሎች ነፃ እስከሚሆን ሕግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል – የሐረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሐረሪ ክልል ከህወሓት ጁንታ ተላላኪዎችና ከኦነግ ሸኔ ተልዕኮ ወስደው ከሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም ሀይሎች ነፃ እስከሚሆን ሕግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሐረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ፓርቲው በመግለጫው እንዳስታወቀው ክልሉ ከጥፋት ተልዕኮ ፈፃሚዎች ሙሉ ለሙሉ ነፃ እንዲሆን እየተሰራ ነው።

“አሁን የምንገኝበት የፖለቲካ መድረክ ሀገር አፍራሽ ከሀዲዎች እየፈረሱ የሚገኙበት ታሪካዊ መድረክ” ነው ብሏል ፓርቲው።

የግፈኞች ፀሀይ እየጠለቀች በምትገኝበት በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ወገን ከሀዲውና ወንበዴው ህወሓትና የጥፋት አጋሮቹ በሌላ ወገን የሚፋለሙበት አውደውጊያ ላይ እንገኛለን ነው ያለው።

የህዝብና የሀገር አለኝታ በሆነው የመከላከያ ኃይል ላይ የተፈፀመው ክህደት አሳፋሪ ነው ብሏል።

አሸባሪ ቡድኑን በያለበት በማደን በሕግ ፊት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ እየተሰራ ይገኛል ሲልም ገልጿል።

የሐረሪ ክልል ከህወሓት ጁንታ ተላላኪዎችና ከኦነግ ሸኔ ተልዕኮ ወስደው የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም ሀይሎችና የጥፋት ተልዕኳቸውን ከሚደግፉ ርዝራዦቻቸው ሙሉ ለሙሉ ነፃ እስከሚሆን ድረስ ሕግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል።

የክልሉ ነዋሪዎች የአካባቢውን ሰላም በንቃት በመጠበቅ ከከሀዲው የሕወሓት ጁንታ ተላላኪዎችና ከኦነግ ሸኔ ተልዕኮ ወስደው የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሠላም ሀይሎችን ለፀጥታ አካላት በማጋለጥ እና ጥቆማ በመስጠት የማይተካ ሚናውን እንዲወጡም ጥሪውን አስተላልፏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.