Fana: At a Speed of Life!

15ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ህዳር 24 በአዲስ አበባ ይከበራል- ጨፌ ኦሮሚያ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 22፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 15ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ህዳር 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚከበር የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶ አስታወቁ።
በዓሉ “እኩልነትና ህብረ ብሄራዊነት ለጋራ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች እንደሚከበርም ገልፀዋል።
ህዳር 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የተለያዩ ክልሎች እንግዶች እና የህብረተሰብ ተወካዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ እንደሚከበር አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ በክልሉ በሚገኙ ዞኖች እና ወረዳዎችም በዓሉ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት እንደሚከበርም አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል።
በዚህም በህግ የማስከበር ዘመቻ ላይ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ደም መለገስ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም እና የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ እንዲሁም ለቀጣይ ዓመት የችግኝ ተከላ ራስን በማዘጋጀት ይከበራልም ነው ያሉት።
በተጨማሪም በኮሮና ቫይረስ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በማገዝ፣ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት እና በሌሎችም የበጎ አድራጎት ተግባራት እንደሚከበርም ተናግረዋል።
በዓሉ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ልዩነቶችን በማንፀባረቅ ብሄር ብሄረሰቦችን የሚያራርቅ ሳይሆን፤ አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑንም ነው የተናገሩት።
አያይዘውም የሀገር መከላከያ ሰራዊት በጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ላይ ለተቀዳጀው ድልም ለመላው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክትም አስተላልፈዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡

ለተንቀሳቃሽ ምስሎች  የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.