Fana: At a Speed of Life!

የአብሮነት እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ወደ ፊት ማራመድ ይገባል – አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአብሮነትና የአንድነት እሴቶች ይበልጥ በማጠናከር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ወደ ፊት ማራመድ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ተናገሩ።

ይህን ያሉት የህብረ ብሄራዊ አንድነት ችቦ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ጋምቤላ ክልል ሲገባ አቀባበል በተደረገበት ወቅት ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ የህወሓት ጁንታ ሲያራምደው የነበረውን የከፋፋይ አስተሳሰብ በማስወገድ አንድነትንና አብሮነትን የመገንባቱ ተግባር ሊጠናከር ይገባል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነታቸውንና አብሮነታቸውን በማጠናከር የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥና የብልጽግና ጉዞ ወደ ፊት ማራመድ እንዳለለባቸውም ተናግረዋል።

የህብረ ብሄራዊ አንድነት ችቦ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በቅብብሎሽ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል እንዲከበር የተወሰነው በህዝቦች መካከል ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን አንድነትና ወንድማማችነት ለማጠናከር መሆኑን አቶ ኡሞድ አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ዘርፈሸዋል ንጉሴ የህብረ ብሔራዊ አንድነት ችቦውን ለጋምቤላ ክልል ሲያስረክቡ “ኢትዮጵያ ለሁሉም የምትበቃ ቤታችን፣ ከለላ እናታችን ናት” ብለዋል።

የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ጁል ናጋል በበኩላቸው ባለፉት 27 ዓመታት ህዝቦችን ለመለያየት ሲሰበክ የነበረውን ከፋፋይ አስተሳሰብ በማስወገድና አንድነትን በማጠናከር የተጀመረው ልማት ለማስቀጠል በጋራ መረባረብ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ታጅቦ ትናንት ጋምቤላ ከተማ ለደረሰው የህብር ብሄራዊ አንድነት ችቦ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች አቀባበል መደረጉን ኢዜአ ዘግቧል።

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.