የሀገር ውስጥ ዜና

የብሄር ብሄረሰቦች ቀን እንደ እስከዛሬው ለይስሙላ ሳይሆን እኩልነትና ህብረ ብሄራዊ አንድነት በተጠናከረበት መልኩ ይከበራል – አቶ አደም ፋራህ

By Abrham Fekede

December 02, 2020

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዘንድሮው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን እንደ እስከዛሬው ለይስሙላ ሳይሆን እኩልነትና ህብረ ብሄራዊ አንድነት በተጠናከረበት መልኩ እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

አቶ አደም ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፌደራሊዝምን ሲነግድበት የነበረው የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን ድል በተደረገበት ማግስት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገውም አንስተዋል።

ለ15ኛ ጊዜ የፊታችን ህዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአዲስ አበባ እና በሌሎችም ክልሎች በደማቅ ሁኔታ ይከበራል ብለዋል፡፡

በዓሉ እንደ ከዚህ ቀደሙ ህዝብ በተሰበሰበበት ሳይሆን የደም ልገሳ መርሃግብር፤ ሲምፖዚየምና የፓናል ውይይቶችን ጨምሮ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችንና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበርም ገልጸዋል።

ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት አንጻርም በአንድ ክልል ከተማ ሳይሆን በአዲስ አበባ የፌደሬሽን ምክር ቤት ከሚያዘጋጃቸው ፕሮግራሞች ባሻገር በዘጋቢ ፊልም መልክ የብሄር ብሄረሰቦችን ሁነት በሚገልጽ መልኩ እንደሚቀርብም አንስተዋል።

አፈ ጉባኤው አያይዘውም የዘንድሮው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል “እኩልነትና ህብረ ብሄራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል ይከበራልም ነው ያሉት።

የበዓሉ ማጠናቀቂያ የሆነው ህዳር 29 ቀን በወንድማማቾች ፓርክ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል፡፡

በጸጋዬ ንጉስ