Fana: At a Speed of Life!

መንግስት በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሰራ ነው – ወ/ሮ ሙፈሪያት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስት በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።

“ወደ ሱዳን የተሰደዱ ንጹሃን ዜጎችን የመመለስና የማቋቋም ስራ ይሰራል” ብለዋል።

ሚኒስትሯ ለአውሮፓ ሕብረት የቀውስ ጊዜ አስተዳደር ኮሚሽን ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺች ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ ለማመቻቸት እያከናወነቻቸው ባሉ ተግባራት ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።

በገለጻቸው መንግስት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የሕወሓት ቡድን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሚያስነሳቸው ግጭቶች ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ በርካታ ዜጎችን የመመለስና የማቋቋም ስራ መሰራቱን አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን ለመመለስና ለማቋቋም የልምድ ማነስ እንደሌለ ገልጸዋል።

ከተሰደዱት መካከል ማንነትን መሰረት ባደረገ ጭፍጨፋ እጃቸው ያለበት ተጠርጣሪዎች ሊኖሩ እንደሚችሉና ጉዳዩን የማጣራት ስራ እንደሚከናወን የማሳወቅ ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ ዜጎችን ያከበረና ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የመመለስ ተግባር እንደሚከናወን ጠቅሰዋል።

የአውሮፓ ሕብረት የቀውስ ጊዜ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺች በበኩላቸው የሕግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ ወደ ሱዳን ለተሰደዱ ኢትዮጵያውያን አራት ሚሊየን ዩሮ መመደቡን መግለፃቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የአውሮፓ ሕብረት በስደተኞች ጉዳይ ላይ ላለፉት በርካታ ዓመታት ከመንግስት ጋር እየሰራ መሆኑንና የሚያደርገው ድጋፍም አውሮፓ ያላትን አጋርነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በተሰጣቸው ማብራሪያ ያለውን ሁኔታ መረዳት እንደቻሉ ገልጸው፤ በሱዳን በሚኖራቸው ቆይታ ስደተኞቹን እንደሚጎበኙና በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር እንደሚመክሩ ጠቁመዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.