Fana: At a Speed of Life!

ኪም ጆንግ ኡን በሃገራቸው የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ ጥለውት የነበረውን እገዳ ማንሳታቸውን አስታወቁ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ፒዮንግያንግ አቋርጣው የነበረውን የኒውክሌር ፕሮግራም በአዲስ መልክ እንደምትጀምር አስታወቁ።

ኪም ለተወሰነ ጊዜ አግደውት የነበረው የኒውክሌር ማበልጸግና የመካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ በቅርቡ እንደሚጀመር ገልጸዋል።

አሜሪካ በኒውክሌር ድርድሩ ዙሪያ አዲስ ሃሳብ ይዛ አለመቅረቧና ከደቡብ ኮሪያ ጋር የምታካሂደውን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ መቀጠሏ ለኪም ሃሳብ ምክንያት ነው ተብሏል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ሰሜን ኮሪያ አዲስ መሳሪያዋን በቅርቡ ለዓለም ታሳያለች ነው ያሉት።

አዲሱ የፒዮንግያንግ እቅድ ተፈጻሚ የሚሆነው ግን በአሜሪካ ድርጊትና እንቅስቃሴ ላይ ተወስኖ መሆኑንም ኪም ተናግረዋል።

በንግግራቸው ፒዮንግያንግ ለድርድር በሯ ክፍት መሆኑንም አስረድተዋል።

ከኪም ንግግር በኋላ አስተያየት የሰጡት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኪም ቀጠናውን ከኒውክሌር ነጻ ማድረግ የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውሰዋል።

አያይዘውም ኪም ቃላቸውን ይጠብቃሉ ብየ አምናለሁ ነው ያሉት ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በበኩላቸው፥ ሰሜን ኮሪያ ከግጭትና ጦርነት ይልቅ ሰላምና ብልጽግና ምርጫዋ እንደሆነ አስባለሁ ብለዋል።

ኪም ጆንግ ኡን ከዚህ ቀደም ዋሽንግተን የፒዮንግያንግን ፍላጎት የማታሟላ ከሆነ አዲስ መንገድ እፈልጋለሁ ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ተንታኞች ሰሜን ኮሪያ ከመካለኛ ጀምሮ የተከለከሉ ሃገር አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ዳግም ልትሞክር እንደምትችል እየገለጹ ነው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ እና አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.