Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል ከ18 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጋምቤላ ክልል ፑኝውዶ ከተማ ከ18 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የውሃ ፕሮጀክቱን በመረቁበት ወቅት በክልሉ ቀደም ሲል  ተጀምረው በተለያዩ ምክንያቶች ያልተጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቅሰው የክልሉ መንግስት የዚህ ዓመት ስራ ትኩረት ነባር ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ከተመረቀው የፑኝውዶ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ በተጨማሪ የስድስት ከተሞች የውሃ ፕሮጀክቶች በቅርቡ እንደሚመረቁ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

በፑኝውዶ ከተማ ባለፉት ዓመታት ሲነሱ የነበሩት የመብራትና የንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግሮች በመቃለላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የክልሉ ውሃና መስኖ ልማት ምክትል ኃላፊ አቶ አቡላ ኞች በበኩላቸው በፑኝውዶ ከተማ የተመረቀው የውሃ ፕሮጀክት በአንድ ቋት የንጹህ መጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ፕሮግራም ከ88 ሚሊየን ብር በላይ  ወጪ እየተገነቡ ከሚገኙት 71 የውሃ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቁም ከ48 ሺህ በላይ ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.