Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ጀርመን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቲፈን አኦር የተመራ ልዑካን ቡድን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

በውይታቸውም ሁለቱ ሀገራት ቀደምም ሲል የተለያዩ ስምምነቶችን እንደተፈራረሙና በአብዛኛው በኢኮኖሚ፤ በአየር መንገድ እና በተለያዩ መስኮች እንደነበሩ በመጥቀስ ያለውን ግንኙነት በማስፋት በሁሉም መስክ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቲፈን አብራርተዋል፡፡

በፖለቲካው መስክም በሚኒስትሮች ደረጃ በርካታ ውይይቶች እንዳሉና ይህም የበለጠ እንደሚጠናከር የጠቆሙት አምባሳደር ስቲፈን የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ እንደሚረዱና ያላቸውን የሁለትዮሽና ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች የማጠናከር ፍላጎት በመግለፅ የሚያደርጉትን ሰብዓዊ እርዳታ እንዲሚጨምሩ እና አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሩ አያይዘውም በግጭቱ ሳቢያ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም እንዲሁም የሚዲያ ተቋማት እገዳን የተመለከቱ ችግሮች እንዳሉ በተለያዩ መንገዶች ይነገራልና ይህ ምን ያህል እውነት ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡

ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው ጀርመን ለኢትዮጵያ ለምታደርገው ሁለንተናዊ ትብብር አመስግነው፣ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ረጀም ጊዜ ያስቆጠረና ግንኙነቱም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካው መስክ እንደሆነ ጠቁመው ይህንን ግንኙነት እና ድጋፍ አሁንም ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

አክለውም አሁን በኢትዮጵያ ካለው ሁኔታ አንፃር ለዜጎች መሰረታዊ ፍላጎቶችና ዲሞክራሲን ለማስፈን መንግስት ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት እየሰራ እንደሆነ በመግለፅ ይህን የሚፈታተኑ ችግሮች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

በዚህም የሕውሓት ቡድን በከፍተኛ ሁኔታ የኢትዮጵያን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍና በርካታ ችግሮች ሲፈጥር እደቆየ ጠቅሰው በሰላማዊ መንገድ ለመወያየት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ከለውጡ በተቃራኒ በመቆም ንፁሃን ዜጎችንና ወታደሮችን በመግደል በኃይል ስልጣን ለመያዝ በማሰቡ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስፈን እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የህግ ማስከበር ስራው በመጠናቀቅ ላይ ስለሆነ የሚቀረው ነገር የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባትና ክልሉን ማጠናከር እንደሆነ ጠቁመው መንግስት ክልሉ ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ኑሮው እንዲመለስ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡

ሕውሓት ሀገር ወስጥ ከማሸበር አልፎ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ሀገራት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በትክክል እንዳይረዱ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ቡድን የሽብር ተግባሩን በተለያዩ ክልሎች በተላላኪዎች በኩል በማስፋትና በመፈፀም በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ሲፈጥር መቆየቱን ዶክተር ነገሪ አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም የታገደ የሚዲያ ተቋም አለመኖሩንና ርምጃው የተወሰደው የተዛባ መረጃ ባሰራጨ ግለሰብ ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የስደተኞች አያያዝን በተመለከተ አስፈላጊው እርዳታ እየተደረገላቸውና የተፈናቀሉ ዜጎችንም መልሶ ለማቋቋም እተሰራ በመሆኑ እየተሰራጨ ያለው መረጃ ከእውነት የራቀ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ በዴሞክራሲ ስም ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲዘርፍና ሲያሰቃይ የነበረው አምባገነኑ ሕውሓትን ለፍርድ በማቅረብ የህግ የበላይነትን በማስፈን የህዝቦችን መብትና ፍላጎት ማስከበር እንደሆነ መግለጻቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.