Fana: At a Speed of Life!

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱ በምእራብ እዝ ሆስፒታል ለሰራዊቱ አባላት የሚደረገውን የህክምና እርዳታ ተመለክተ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርድ በምእራብ እዝ ሆስፒታል ለሰራዊቱ አባላት የሚደረገውን የህክምና እርዳታ ተመለክተ።

ሰሞኑን በምዕራብ ትግራይና በአጎራባቹ የአማራ ክልል ተዘዋውሮ የምርመራ ስራውን ሲያከናውን የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ የመጀመሪያውን ዙር የመስክ ምልከታ ማጠናቀቁን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የመርማሪ ቦርዱ አባላት የመስክ ምልከታቸውን ሲያገባድዱ በባህርዳር ከተማ የምዕራብ እዝ  ሆስፒታል ተገኝተው በተደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ ቆስለው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ተመልክተዋል።

በተደረገላቸው ፈጣን የህክምና አገልግሎትና ተገቢ እንክብካቤ አብዛኞቹ ታካሚዎች እያገገሙ መሆኑን የሰራዊቱ አባላት አስረድተው፤ የመርማሪ ቦርዱ አባላት በአካል ተገኝተው ስለአበረታቷቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ እና የምዕራብ እዝ ሆስፒታል ሎጀስቲክስ ኃላፊ ኮሎኔል ሰብለ ሙሉጌታ የመርማሪ ቦርዱ አባላት በመካከላቸው ተገኝተው ስለጎበኟቸው አመስግነዋል።

አደጋው ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ እቅድ በማውጣት ከክልል እስከ ወረዳ የአደጋ ምላሽ ኮሚቴ በማቋቋም መደበኛው የጤና አገልግሎት ሳይስተጓጎል ስኬታማ ስራ መሰራቱን አስረድተዋል።

የቦርዱ አባላትም የሰራዊቱ አባላት ባደረጉት ተጋድሎ የኢትዮጵያን ህዝብ ለድል በማብቃታቸው እንዲሁም፤ የክልሉ ጤና ቢሮ የስራ ኃላፊዎችና የጤና ባለሙያዎች በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ስለማገልገላቸው ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይ የክልሉን የጤና አገልግሎት ለመደገፍ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት መረጃ በማቅረብ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ የመጀመሪያውን ዙር የመስክ ምልከታ ሙሉ ሪፖርት በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.