Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በ2017 ለዜጎቿ ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እየሰራች ነው- ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም ለዜጎቿ ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ አቅዳ እየሰራች መሆኑን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለፁ።

ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በዛሬው እለት በዌቢናር በተካሄደው የዩይትድ ኪንግደምና የአፍሪካ የኢነርጂ ሚንስተሮች ሲምፖዚየም ላይ ነው ይህንን የተናገሩት።

በሲምፖዚየሙ ላይ የኢትዮጵያ፣ የሞሮኮ፣ የግብፅ፣ የሞዛምቢክና የሞሪታኒያ ሀገራት የኢነርጂ ሚንስትሮች ንግግር አድርገዋል።

183 ባለድርሻዎችም የዌቢናር ውይይቱን መታደማቸውን ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚንስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሲምፖዚየሙ ላይ ንግግር ያደረጉት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለም፥ ኢትዮጵያ እስካሁን 60 በመቶ የሚሆኑ ዜጎቿ  የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ገልፀዋል።

የኃይል አቅርት ችግሩ ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን እያስከተለ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ፥ ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር ኢትዮጵያ የተለያዩ  እቅዶችን በማውጣት እየሰራች መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም በሚቀጥሉት 10 ዓመት ኢትዮጵያ 20 ሺህ ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር አቅዳ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

በ2017 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ በ2025) ደግሞ ኢትዮጵያ በግሪድና በኦፍ ግሪድ ለዜጎች ሙሉ በሙሉ ሃይል ለማቅረብ ያለመች መሆኑን ጠቁመዋል።

ዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪና ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ በመሆኑ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ሃገራት ባለሃብቶች በዘርፉ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በኢነርጂ ሴክተሩ ላይ ማሻሻያዎችን በማድረጓ ከውጭ ለሚመጡ ኢንቨስተሮች ምቹ አሰራር መዘርጋቱንም አብራርተዋል።

በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ በጂኦተርማል፣ በንፋስ፣ በሶላርና በባዮ ኢነርጂዎች የሏትን እምቅ  አቅም ወደ ሃይል ለመቀየር ኢንቨስት እንዲያደርጉም ለዩናይትድ ኪንግደም ባለሃብቶች ጥሪ አድርገዋል።

በዚህ የዩናይትድ ኪንግደምና የአፍሪካ የኢነርጂ ሚንስትሮች የዌቢናር ስብሰባ ላይ የኢንግሊዝ ሃገር የልማት ተራድኦ ድርጅት በኦፍግሪድ ሃይል አቅርቦት ስራ ላይ የሚያደርገውን የፋይናንስ ድጋፍም በዚሁ ጊዜ ተነስቷል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.