Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ እሁድ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካን ኦሊምፒክ ስፖርቶች በበላይነት የሚመራው የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር (አኖካ) አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን የፊታችን እሁድ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ያካሂዳል፡፡
ጉባኤው በአህጉሩ የኦሊምፒክ ስፖርቶች ዙሪያ አስፈላጊ ናቸው በሚባሉ ጉዳይች ላይ ይወያያል፡፡
አኖካ ከወራት በፊት ባሳለፈው ውሳኔ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአህጉሩን ከፍተኛ የስፖርት ሽልማት (ኦርደር ኦፍ ሜሪት) ተሸላሚ እንዲሆኑ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
በዘንድሮው ጉባኤ ላይ ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከልም አንዱ ይህን ሽልማት የሚያበረክትበት ፕሮግራም ነው፡፡
ሽልማቱን በማስመልከት ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ ቤራፍ “ ውሳኔው የግለሰቦች ሳይሆን የአኖካ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ነው ብለዋል፡፡
“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአፍሪካ ስፖርት እድገት ትልቅ ሚና ለሚጫወተው የኢትዮጵያ ስፖርት ላሳዩት ድጋፍ እና ለኦሊምፒክ መንደር ግንባታ ላደረጉት የ3 ቢሊየን ብር ድጋፍ የአህጉሩን ከፍተኛ የስፖርት ሽልማት ለማበርከት ወስነናልም”ነው ያሉት፡፡
የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ዋና ፀሐፊ አህመድ አብዱልቃሲም በበኩላቸው ኢትዮጵያ አሁን በስፖርቱ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም በኢትዮጵያ ጥሩ መሰረተ ልማቶች እንዳሉ መገንዘባቸውን በመጥቀስም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ያለውን መሰረተ ልማት ለማማሻል የሚረዳ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
“ሌሎች የአፍሪካ መሪዎችም ከዚህ እንዲማሩ ስለምንፈልግ ይህን ታላቅ ሽልማት የምንሰጣቸውም” ብለዋል ዋና ፀሐፊው፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ አሁን ከላው የኮቪድ የጉዞ ክልከላ ጋር በተያያዘ ብዙ ሰው ላይመጣ ይችላል የሚል ስጋት እንደነበረባቸው አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጅ በጠቅላላ ጉባኤው ከ52 ሀገራት ለዘገባ የሚመጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ250 በላይ ሰዎች ለመታደም ማረጋገጫ መስጠታቸውንና አብዛኛዎቹም አዲስ አበባ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
በአብዱ ሙሐመድ
ተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.