Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 4 ወራት በገጠር የስራ ዕድል ፈጠራ ከ270 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት አራት ወራት በገጠር የስራ ዕድል ፈጠራ 270 ሺህ 320 ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ።

የገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ የ10 ዓመት ዕቅድ እና የ2013 ዓ.ም የአራት ወር የስራ አፈፃፀም ላይ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብትና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሳኒ ረዲ በመድረኩ ላይ፥ የስራ ፈላጊ ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው፤ በኢትዮጵያ ከ10 ሚሊየን በላይ ስራ ፈላጊ ወጣቶች አሉ ብለዋል።

የስራ አጥነቱ ችግር ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳለው በመግለፅ፤ ይህ እንዳይሆንም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ2 እስከ 3 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ወደ ስራ እንደሚገቡ ነው የተናገሩት።

በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኘውን የስራ ፈላጊ ቁጥር ግምት ውስጥ በማስገባት ሃገራዊ የገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ እና የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተቀርፆ ወደ ተግባር መገባቱንም አንስተዋል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ በድምሩ 303 ሺህ የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ192 ሺህ 37 ወንድና ለ78 ሺህ 283 ሴት በድምሩ ለ270 ሺህ 320 ዜጎች ስራ የተፈጠረ ሲሆን የዕቅዱን 99 በመቶ ማሳካት መቻሉም በመድረኩ ተገልጿል።

በግብርና ሙያ ላይ ለመሰማራት ያለው ፍላጎት አነስተኛ መሆን፣ የመሬት አቅርቦት ችግር፣ የፋይናንስ አቅርቦትና ትስስር ማነስ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት እና የመሰረተ-ልማት አቅርቦት በበቂ አለመስፋፋት በገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ የሚታዩ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.