Fana: At a Speed of Life!

የጥላቻና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል በተዘጋጀው ረቂቅ ላይ ያሉ የትርጉምና የይዘት ክፍተቶች መሙላት እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥላቻና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ያሉ የትርጉምና የይዘት ክፍተቶች መሙላት እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
 
በረቂቁ ዙሪያ በዛሬው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህዝብ ውይይት አካሂዷል፡፡
 
በውይይቱ ላይ ይህ ረቂቅ በስሩ ያሉ ዝርዝር ጉዳዮችን በግልጽ በማስቀመጥ ደረጃ ክፍተት እንዳለበት እና ለትርጉም ተገላጭ መሆኑ ተነስቷለ።
 
አሁን ላይ በሀገሪቱ ሀሳብን በነጻነት ማንሸራሸር የሚችሉ የተለያዩ ሀሳቦችንም ማስተናገድ አቅም ያላቸው መገናኛ ብዙሀን እምብዛም ባልተደራጁበት ወቅት ሰው ሀሳቡን የሚገልጽበትን ማህበራዊ ሚድያ ላይ ሰፊ ቁጥጥር ማድረግ የመናገር ነጻነትን እንዳይጋፋ በስጋትነት ቀርቧል።
 
የህጉ ተፈጻሚነት እስከ ምን ድረስ እንደሚጓዝ፣ ሀሰተኛ እና የጥላቻ ንግግሮችን የሚቆጣጠር፣ የሚመረምር እና የሚዳኝው አካል በረቂቁ ላይ በግለጽ አለመቀመጡ ደግሞ የአተገባበር ክፍተትን ሊፈጥር ይችላል ተብሏል።
 
የማህበራዊ ሚዲያ አንዳንዶች ሀሳባቸውን በነጻነት የሚያንጸባርቁበት ሌሎች ደግሞ ግጭትን ለመቀስቀስ የሚጠቀሙበት በመሆኑ ጥፋተኛውን ከንጹሁ ለመለየት ዝርዝር ነጥቦች መካተት እንደሚያስፈልግ ነው በውይይቱ የተነሳው።
 
በተለይም ጥላቻ ሀሳብ እንዳንድ ጊዜም ከስብዕና እና ከስነልቦና ጋር የሚያያዝ በመሆኑ በታሪክ እና በሌሎች ሁነቶች ለጥላቻ እና ለግጭት መንስኤ የሆኑ ሁነቶችን ማረቅ ከተቻለ ረቂቁ አስፈላጊ ላይሆን እንደሚች ተወያዩቹ አንስተዋል።
 
እንዲሁም ረቂቁ በመሻሻል ላይ የሚገኙትን የሽብር እና የመገናኛ ብዙሃን አዋጆች ሊያስቀሯቸው የሚችሉትን ነጥቦች እንዳያካትት ጥንቃቄ መደረግ አለበት ነው የተባለው።
 
ሀገሪቱ ዘንድሮ ታደርገዋለች ተብሎ የሚጠበቀው ሀገራዊ ምርጫ እስኪጠናቀቅ አዋጁ እንዲዘገይ በተሳታፊዎች ተጠይቋል፡፡
 
በተነሱ ጥያቄ እና አስተያየቶች ላይ ምላሽ የሰጡት የፌዴራል ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌድየን ጢሞትዮስ ÷ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከህጉ አላማ ውጪ እንዳይታፈን ታሳቢ ተደርጓል ብለዋል።
 
ከዚህ ባለፈ ግን ሀሳብን በነጻነት መግለጽ መብት ፍጹም መብት ባለመሆኑ በህገመንግስቱም ገደብ ተቀምጦለታል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ይህኛው ረቂቅም በዚህ መሰረት ተግባራዊ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
 
አንድ ሀሰተኛ መረጃ ሀሰተኛ መረጃ መሆኑ በምን ይረጋገጣል ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም ሀሰተኛ መረጃ አልያም ዜና ተሰራጭቶብኛል ብሎ በሚመጣው ግለሰብ በሚቀርቡ መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ በሚደረግ ምርመራ ይረጋገጣል ብለዋል።
 
 
 
በዳዊት በሪሁን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.