የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅትና ትግበራ ምክር ቤት ስብሰባ ተካሄደ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅትና ትግበራ ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሄደ።
በስብሰባው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅትና ትግበራ የአፈፃፀም ሂደት እንዲሁም ረቂቅ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ በዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ትንሹ ቆይታ 4 ዓመት ሲሆን በቆይታቸውም በመጀመሪያው ዓመት በጋራ የሚወሰዱ ኮርሶችን እየወሰዱ ይገኛሉ።
ከዚህ ዓመት ጀምሮም ለ10ኛ ክፍል ሲሰጥ የነበረው የአጠቃላይ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና የሚቀር ሲሆን፥ ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው የትምህርት ህግም ከትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው ጋር ተሳስሮ እንዲሰራ መደረጉ ተገልጿል።
ይህም በየደረጃው ውይይት ከተካሄደበት በኋላ በረቂቅ ህግ ተዘጋጅቶ ይቀርባል ነው የተባለው።
አሁን ላይም የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታውን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አሳትሞ ለማውጣት ቅድመ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።