Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት እና የቻይና ሳይንስ አካዳሚ የአፕላይድ ኢኮሎጂ ኢንስቲቲዩት በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት እና ሽንያንግ ከተማ የሚገኘው የቻይና ሳይንስ አካዳሚ የአፕላይድ ኢኮሎጂ ኢንስቲቲዩት በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን የሚሲዮኑ መሪ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እና የኢንስቲቲዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ዩንቲንግ ፋንግ ተፈራርመውታል፡፡
በስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በጋራ በመተባበር የግብርና ምርምርና የልማት ስራዎችን፣ የአካባቢ እና ሥነ-ምህዳር ምርምር፣ በመስኩ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ነፃ የትምህርት ዕድል እና የገንዘብ ድጋፍ በማፈላለግ የሰው ሀይል አቅም ግንባታ እንዲሁም የአካዳሚክ እና የባለሙያዎች ልውውጥ ለማካሄድ ተስማምተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በመግባቢያ ስምምነቱ የለዩዋቸውን የትብብር መስኮች ለመፈጸም ይረዳ ዘንድም በሻንዶንግ ግዛትዌይፋንግ ከተማ አዲስ በተመሰረተው የዌይፋንግ የዘመናዊ እርሻ እና ኢኮሎጂካል አካዳሚ ግቢ ውስጥ የኢትዮ – ቻይና የግብርና እና አካባቢ የምርምር ማዕከል ለመመስረት እንዲሁም በኢትዮጵያ ተመሳሳይ ማዕከል ለመክፈት መታቀዱ ተገልጿል።
የሚሲዮኑ መሪ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የመግባቢያ ሰነዱን በፈረሙበት ወቅት ስምምነቱ የሃገራቱ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት መገለጫ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የግብርና ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ሚና ቀዳሚ እንደሆነ በተለይም ዘርፉ ከያዘው ሰፊ የሰው ሀይል እና የወጪ ንግድ አንጻር ወሳኝ ድርሻ እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ላይ ለግብርና ትኩረት በመስጠት ዘርፉን ለማልማት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምርታማነቱን በሁለትና በሦስት እጥፍ ለማሳደግ በመንግስት በኩል በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የኢንስቲቲዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ያንቲንግ ፋንግ ፋንግ በበኩላቸው ከኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ጋር ያለውን ትብብር የበለጠ በማጠናከር በክልሉ ብሎም በሃገሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚረዱ ምርምሮችን በማካሄድ የግብርና ምርቶችን ማሳደግ የሚያስችሉ ምርምሮችን ለማድረግ ፍላጎት መኖሩን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም አነስተኛ ማሳ ላላቸው ገበሬዎች መስኖን ተጠቅሞ ምርትን ለማሳደግ የሚረዱ አሰራሮችን ለመዘርጋት፣ የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ አነስተኛ ማሽነሪዎች በማምረት ለተጠቃሚው ለማቅረብ እንዲሁም አካባቢን እና ስነምህዳርን በመጠበቅ አሲዳማ አፈርን አክሞ ለምርታማነት ለማብቃት የሚያስችሉ ምርምሮች ለማከናወን ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን
ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.