Fana: At a Speed of Life!

ባለስልጣኑ የቆጣሪ ጥራት ችግርና ግምታዊ አሞላልን ማስቀረት የሚያስችለውን ዘመናዊ የቆጣሪ ንባብ ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የዘመናዊ የቆጣሪ ንባብ ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

ዘመናዊ የቆጣሪ ንባብ ስርዓቱ ተግባራዊ የተደረገው በባለስልጣኑ የአራዳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስር ባሉ 18 ወረዳዎች ሲሆን፥ በጥቅሉ 47 ሺህ ደንበኞች ላይ ተግባራዊ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

ዘመናዊ የቆጣሪ ንባብ ስርዓቱ የቆጣሪ ጥራት ችግርን እና ግምታዊ አሞላልን ከማስቀረት ባለፈ ደንበኛው የውሃ ፍጆታውን በተጠቀመበት ወር ለመክፈል እንደሚያስችለው እና የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ከማሳለጥ አንጻር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡

የንባብ ስርዓቱ ለዚሁ ተግባር ተብሎ አፕልኬሽን በተጫነባቸው የሞባይል ስልኮች አማካኝነት የሚሰራ ሲሆን፥ ቆጣሪ አንባቢው በደንበኛው ቤት ወይም ድርጅት በሁለት ሜትር ክልል ውስጥ እንዲገኝ ያስገድደዋል፡፡

ይህም በስፍራ ተገኝቶ ትክክለኛ መረጃ እንዲያስገባ ያስችለዋል ሲሉ የባለስልጣኑ የደንበኞች አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ አርጋው ተናግረዋል፡፡

ይህ ዘመናዊ የቆጣሪ ንባብ ስርዓት ተግባራዊ የተደረገው በአራዳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስር በሚገኙ አራዳ ክፍለ ከተከ ወረዳ 1፣8፣9፣10፤ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከወረዳ 1 እስከ 4 (በከፊል) ፤ ቂርቆስ ወረዳ 7 እና 8 ፤ልደታ ክፍለ ከተማ ከወረዳ 3 እስከ 9 እና በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡

በቀጣይም በቀሩት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በሚገኙ የባለስልጣኑ ደንበኞች ላይ ተግባራዊ ያደረጋል ነው የተባለው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.