የሀገር ውስጥ ዜና

የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት 23 የጸረ-ሠላም ኃይሎች ላይ እርምጃ ወሰደ

By Meseret Demissu

December 08, 2020

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 29 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን 23 የጸረ ሠላም ኃይሎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የዞኑ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።

የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ኮሎኔል አያሌው በየነ÷ በዞኑ ዳንጉር ወረዳ ልዩ ስሙ ቁጥር 3 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሠላምን ሲያውኩ በነበሩ ኃይሎች ላይ በተወሰደው እርምጃ 23 ጸረ-ሠላም ኃይሎች መደምሰሳቸውን ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ የጸጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ ከተደመሰሱት የጸረ-ሠላም ኃይሎች በተጨማሪ ለጥፋት ሲጠቀሙበት የነበረ ሶስት የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የጥፋት ቡድን በሠላማዊ መንገድ እጅ እንዲሰጥ በክልሉ መንግሥት ጥሪ መቅረቡን አስታውሰው÷ በጥሪው መሠረት መጠቀም ካልቻለ በዋናው ጁንታ ላይ የተወሰደው የማያዳግም እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አሳስበዋል።

ህብረተሰቡም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የአካባቢውን ሠላም በተደራጀ መንገድ በመጠበቅ ረገድ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።