ዓለምአቀፋዊ ዜና

ጥቁር አሜሪካዊው ሎይድ ኦስቲን በጆ ባይደን የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ታጩ

By Tibebu Kebede

December 08, 2020

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጡረተኛው የቀድሞው ጄኔራል ሎይድ ኦስቲን በተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው መታጨታቸው ተገለፀ።

የሎይድ ኦስቲን ሹመት በአሜሪካ ሴኔት ከፀደቀ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያው አፍሪካ አሜሪካዊ የመከላከያ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብሏል።

በፈረንጆቹ 2016 በጡረታ ከጦሩ ከመሰናበታቸው በፊት የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ አዛዥ የነበሩት ሎይድ ኦስቲን የጆ ባይድን ቀዳሚ እጩ ነበሩ።

ተመራጩ ፕሬዚዳንቱ ጆ ባይደን በዛሬው ዕለት የመከላከያ ሚኒስትሩን እጩነት ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ እየተጠበቀ መሆኑን ፖለቲኮ ታማኝ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ በዘገባው አስፍሯል።

ጆ ባይደን ጥቁር አሜሪካዊ የመከላከያ ሚኒስትር በእጩነት እንዲያቀርቡ ግፊት ሲደረግባቸው እንደነበርም ዘገባው አመልክቷል።

በአሜሪካ ታላቁን ተቋም ለመምራት በዕጩነት የቀረቡት ጄኔራሉ ፔንታጎን ውስጥ እና ከጆ ባይደን ጋር በቅርበት መስራታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡