የትግራይ ክልልን መልሶ ለመገንባት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ክልልን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማህበራት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።
ራሱን ተጋሩ የኢትዮጵያውያን ድርጅት ብሎ የሚጠራው የሲቪክ ተቋም፣ በትግራይ ወቅታዊና መጻኢ ጉዳዮች ዙሪያ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖሊቲካ ፓርቲ አመራሮችና የሲቪክ ማህበራት ጋር ውይይት አድርገዋል።
የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዮሐንስ ጎይቶም በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ግልፅ እና አሳታፊ ለማድረግ በማሰብ ውይይት ማድረግ ማስፈለጉን ገልጸዋል።
ለውጡን ተከትሎ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች እንዲፈቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ማህበረሰቡ ጋር በመተባበር ችግሮቹ እንዲፈቱ እና አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሃገር ሽማግሌዎች፣ ከፖሊቲካ ፓርቲዎች እና ዜጎችን ያካተተ የመማክርት ጉባኤ መቋቋም ስላለበት ለባለድርሻ አካላት ለማስገንዘብ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የትግራይ ህዝብ በተጀመረው የለውጥ ጉዞ ፖሊቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፍትህ እንዲቀዳጅ ተባብረን መስራት አለብን ብለዋል አቶ ዮሐንስ።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል እንዳሉት በትግራይ በሚደረገው መልሶ የማቋቋም ተግባር በክልሉ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ፓርቲ እና የሲቪክ ማህበራት የበኩላቸውን ለመወጣት እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው።
የሲቪክ ማህበራትም በቀጣይ በክልሉ በሚደረጉ የለውጥ ጎዞዎች የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልፀው ፓርቲውም ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው የህወሓት ጁንታ በትግራይ ክልል ለሶስት አስርት አመታት ያደረሰውን ችግር መፍታት የሚቻለው ተቀራርቦ በመነጋገር መሆኑን ጠቅሰዋል።
የትግራይን ህዝብ ችግር መፍታት የሚቻለው የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም ብቻ ሳይሆን የሲቪክ ማህበራትንም በማደራጀት እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!