ኤጀንሲዉ ለዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰራዉን ደህንነቱ የተጠበቀ የሰዉ ሃይል አስተዳደር ስርዓት አስመረቀ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 30፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ለዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰራዉን ደህንነቱ የተጠበቀ የሰዉ ሃይል አስተዳደር ስርዓት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት አስመርቋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ስራዉ ብዙ እንደተደከመበት ጠቁመው÷ ኤጀንሲዉ ላደረገዉ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከዚህ ባለፈ ቴክኖሎጂዉን በስትራቴጂ እና በፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ከመምራት ጀምሮ በተሟላ መልኩ አገልግሎቱን ለማግኘት እንዲቻል ተከታታይ ድጋፍ የማድረግ ስራም ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የዘመነ አገልግሎትን ለመስጠት የሰዉ ሃይልን በእዉቀት፣ በመረጃ እና ቴክኖሎጂ መደገፍ እና መምራት ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ነን ያሉት አቶ ደመቀ ቴክኖሎጂው ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቀደሞ ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባ መሰረታዊ ጉዳይ እንደነበርም አውስተዋል፡፡
የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸዉ÷ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተሰጠዉን ተግባር እና ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት ዘመኑ ከሚፈልገዉ ቴክኖሎጂ ጋር ተጣጥሞ እና ታግዞ ስራዉን መስራት ግዜው የሚጠይቀው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ልማት እጅግ አስፈላጊ መሆኑት የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ ÷በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የለማዉ ሶፍትዌር መረጃን ከማደራጀት ባሻገር የመረጃ ልዉዉጡን የሚያሳልጥ ነዉ ብለዋል፡፡
ቴክኖሎጂዉ ፍትሃዊ የሆነ አገልግሎትን ለመስጠት፣ ለተደራሽነት፣ የሰዉ ሃይል ልማቱን በታቀደ መልኩ ለማከናወን እጅግ ጠቃሚ መሆኑንም አምባሳደር ብርቱካን ገልጸዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይድነቃቸዉ ወርቁ በበኩላቸው÷ ሶፍትዌር በተቋማት ተግባራዊ ማድረግ የመጀመሪያዉ ግብ ቢሆንም ዋናዉ ስራ ግን ቀጣይነት እና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ስራ ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ኤጀንሲዉ ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ የሚስራቸዉ ስራዎች መኖሩን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በቀጣይም ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መሰል የቴክኖሎጂ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
የኤጀንሲዉ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንተነህ ተስፋዬ በበኩላቸው÷ በሃገራችን በርካታ ከቴክኖሎጂ ጋር የተቆራኙ ተቋማት ቢኖሩም ደህንነቱ የተጠበቀ የሰዉ ሃብት ሲስተም ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀዳሚ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ተቋማትን በቴክኖሎጂ ከማብቃት ባሻገር በግዢ፣ ፋይናንስ እና ሰዉ ሃይል አስተዳደር ላይ ተከታታይ የሆነ ስልጠና መስጠት እንደሚገባም ዶክተር አንተነህ ተስፋዬ አሳስበዋል፡፡
በምረቃ ስነስርአቱ ላይ ገለጻ ያደረጉት የኤጀንሲዉ የሳይበር ቢዝነስ እና ማናጅመንት ዲቪዥን የማዕከል ሃላፊ አቶ አኑዋር የሱፍ ይህ ስርዓት ከእቅድ ጀምሮ የቅጥር፣ ዝዉዉር ፣እድገት ፣ዓመታዊ የስራ ፍቃድ፣ የስራ ስንብት ክንዉኖችን ዘመናዊ በሆነ መልኩ የሚከዉን ስርዓት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኤጀንሲዉ ለዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰዉ ሃብት መረጃ ስርዓት እና አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን የሚረዳ “የሰዉ ሃይል አስተዳደር ሲስተም” አልምቶ ለአገልግሎት በማብቃቱ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የምስጋና የምስክር ወረቀት መሰጠቱን ከኢመደኤ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል
https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!