Fana: At a Speed of Life!

ቋሚ ኮሚቴው በዋጋ ግሽበት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አሳሰበ

አዲስ አበባ፤ ኅዳር 30 ፤2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋጋ ግሽበት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የገንዘብ ሚኒስቴርንና የተጠሪ ተቋማቱን የ2013 በጀት አመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

ሪፖርቱን ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ ሀገራዊ አጠቃላይ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ የ20 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አመታት ባለሁለት አሀዝ እድገት የተመዘገበ ቢሆንም በ2012 በጀት ዓመት የኮሮና ቫይረስ ተፅእኖን በመቋቋም 6 ነጥብ 1 የምጣኔ ሃብት እድገት መመዝገብ መቻሉን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

ዶክተር እዮብ ጨምረውም የታክስ ማበረታቻ አሰጣጥ ከጠቅላላ ሀገር ውስጥ ምርት ድርሻው 7 በመቶ ደርሶ የነበረ ቢሆንም በተደረገው የታክስ ማሻሻያ ወደ 5 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በዚህም 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ማዳን መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በሀገሪቱ ያጋጠመውን የኢኮኖሚ ችግር ግምት ውስጥ ያስገባ ስራ እየሰራ መሆኑ፣ የውጭ ንግድና የሴቶችን አቅም ከማብቃት አኳያ ያሉት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ገልጿል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ ያየሽ ተስፋሁን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማቱ በዋጋ ግሽበት ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ከተጠሪ ተቋማት ጋር ተደጋግፎ ከመስራት አኳያ ክፍተት መኖሩን የገለጹት ሰብሳቢዋ፣ የመኪና ግዥ ዋጋ ግሽበት፣ የግዥ ማዕቀፍ እንዲሁም ከቀረጥ ነፃ የሆኑ እቃዎችን በተመለከተ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

በቋሚ ኮሚቴው በእጥረት የተጠቀሱና በትኩረት ሊሰሩ የሚገባቸውን ነጥቦች በእቅዳቸው አካተው እንደሚሰሩባቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በምላሻቸው ማብራራታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.