ኢትዮጵያ በዓለም ጤና ድርጅት የሚመራውን የኮቪድ-19 ህክምና ምርምር ተቀላቀለች
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ኢትዮጵያ በዓለም ጤና ድርጅት የሚመራውን የኮቪድ 19 ህክምና ምርምርን ተቀላቀለች።
የአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አለምሰገድ አብዲሳ የህክምና ሙከራ ምርምሩ ለሌላ ህክምና ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ መድኃኒቶች ለኮቪድ-19 ህክምና ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ የሚፈተሽበት መሆኑን አንስተዋል።
ኢንስቲትዩቱ እያከናወናቸው የሚገኙ የምርምር ስራዎችን በተመለከተ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የዓለም ጤና ድርጅት ይህንን የሚያግዝ የትብብር መድረክ በማዘጋጀት የኮቪድ-19 ህክምና ክትባትና ምርመራ ዘዴዎችን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ላይ ይገኛል።
በዚህ ትብብር ከ30 በላይ ሀገራትና 500 ሆስፒታሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ኢትዮጵያም በአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲቲዩት አማካኝነት በዓለም ጤና ድርጅት የሚመራውን የኮቪድ-19 ህክምና ምርምር በመቀላቀል በአፍሪካ ከግብጽና ደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ሶስተኛዋ ሀገር መሆኗን ኢዜአ ዘግቧል።