Fana: At a Speed of Life!

የዘንድሮ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 12 ሺህ 500 ዝቅ መደረጉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ነገ ምዝገባ በሚጀምረው 20ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 12 ሺህ 500 ተሳታፊዎች እንደሚካሄድ ተገለፀ።

የኮቪድ-19 ቅድመ ጥንቃቄዎችን ተቀዳሚ በማድረግ ጥር 2 2013 ዓ.ም የሚካሄደው 20ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ምዝገባ በነገው እለት እንደሚጀመርም ተገልጿል።

የውድድሩ ምዝገባ ከታህሳስ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተሳታፊዎች በያሉበት አሞሌን በመጠቀም እንዲያካሂዱ ዝግጅቱ መጠናቀቁን የገለጸው ታላቁ ሩጫ፤ የመመዝገቢያ ዋጋውም 450ብር መሆኑን ገልጻል።

የዚህ ዓመት ታላቁ ሩጫ የውድድር መነሻ መስቀል አደባባይ ሲሆን መድረሻው ደግሞ አትላስ አካባቢ መሆኑንም ታላቁ ጫ በኢትዮጵያ በሰጠው መግለጫው አስታውቋል።

በተጨማሪም የዓለም አቀፍ ተሳታፊዎችን ለማካተት ውድድሩ በሚካሄድበት ተመሳሳይ ቀን በቨርቹዋል ውድድር በያሉበት ተሳታፊ እንዲሆኑና የ20ኛውን ዓመት ክብረ በዓል አብረው እንዲያከብሩ ቅድመ ሁኔታ መጠናቀቁንም ገልጿል።

የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያ መሰረት ከቀድሞ ተሳታፊ 25 በመቶ ብቻ አሳታፊ የሚደርገው ታላቁ ሩጫ  የኮቪድ-19 ቅድመ ጥንቃቄዎች ተግባራዊ እንብደሚያደርግም ተገልጿል።

በዚህም መሰረት ውድድሩ የሚጀመረው በሶስት የተለያዩ ማዕበሎች ማለትም አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለሞችን በመጠቀም እንደሚሆን ነው ታላቁ ሩጫ የገለጸው።

ሶስቱ ማዕበሎች ወደ መስቀል አደባባይ የሚመጡበት አቅጣጫ በየቲ-ሸርት ቀለሙ ተለያይቶ የተሰየመ ነው ተብሏል።

እያንዳንዱ ማዕበልም ማህበራዊ ርቀትን ለማስጠበቅ ሲባል በሦስት እና በአራት ቡድን ይከፈላል።

ሩጫው በሶስት የተለያዩ መነሻ ሰዓት የሚደረግ ሲሆን ተሳታፊዎች የሚጀምሩበትን ሰዓት እና አብረው የሚሮጡትን ቡድን ለመለየት ከሩጫ ቲ-ሸርታቸው ጋር አብረው የሚወስዱት የደረት የመሮጫ ፊደል ጠቋሚ እንደሚደረግ ነው የተጠቀሰው።

እያንዳንዱ ተሳታፊ ከሚመርጠው የቲ-ሸርት ቀለም ባሻገር የመወዳደሪያ የደረት ቁጥር በፊደል እንደሚወስድ ገልጸው ተሳታፊዎች የመሮጫ ቲ-ሸርታቸውን ሲወስዱ አብሮ የሚሰጣቸውን የአፍና አፍንጫ ጭንብል የውድድሩ መነሻ የመሰበሰቢያ ቦታና ውድድሩን ከጨረሱ በኋላ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ተጠቅሷል።

ከዚያም በተጨማሪ ተሳታፊዎች መወዳደሪያ ቦታው ላይ እንደደረሱ እያንዳንዱ ተሳታፊ የሰውነት ሙቀት ልኬት የሚደረግለት ሲሆን፥ በውድድሩ መነሻና መድረሻ የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር ይቀርባል ብሏል።

ወፎችን ታሳቢ ያደረገ የኃይል መሰረተ ልማት የ2013 የሩጫ መልዕክት ሲሆን “በርድ ላይፍ አፍሪካ” የነጩ ጆፌ አሞራ ፕሮጀክት የዚህ መልዕክት አስተላላፊና አጋር ድርጅት መሆኑ ተነግሯል።

ተሳታፊዎች ውድድሩ ሊካሄድ 10 ቀናት ሲቀሩት የመወዳደሪያ ቲ-ሸርት የመሮጫ የደረት ቁጥር ፊደል እና ጭምብል ምዝገባ ሲያደርጉ በመረጡዋቸው የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎች በመሄድ መቀበል እንደሚኖርባቸው አሳስቧል።

የዘንድሮ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አጋር ድርጅቶች ቶታል እንደወትሮ የስያሜ ስፖንሰር ሲሆን፤ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት- የሚዲያ አጋር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ እና ሌሎች ድርጅቶች መሆናቸውን ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.