Fana: At a Speed of Life!

የአምራች አድራሻቸው የማይታወቅና ተጭበርብረው የተመረቱ 27 የምግብ ዓይነቶች ገበያ ላይ መኖራቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በተደረገ ቅኝት የአምራች አድራሻቸው የማይታወቁና ተጭበርብረው የተመረቱ 27 የምግብ ዓይነቶች ገበያ ላይ እየዋሉ መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣን መስሪያቤቱ የአምራች ድርጅቶቻቸው አድራሻ የማይታወቁ፣ ተመሣሥለውና ተጭበርብረው የተመረቱ የምግብ ምርቶች ገበያ ላይ እየዋሉ መሆኑን ባደረገው የገበያ ቅኝት ማግኘቱን አስታውቋል።

በዚህ የገበያ ቅኝት ቁጥጥር የታሸጉ ምግቦች የተሟላ የገላጭ ጽሁፍ የሌላቸው፣ አስገዳጅ ብሔራዊ ደረጃን ያላሟሉ፣ የአምራች ድርጅቶቻቸው የማይታወቅና ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው እንዲሁም የአምራች አድራሻ እና መለያ ቁጥር የሌላቸው ምርቶች ማግኘቱን አስታውቋል።

በተጨማሪም የመጠቀሚያና የተመረተበት ጊዜ በትክክል ያልታተሙ የተለያዩ ምርቶች መገኘታቸውን ጠቅሶ፥ ኤሊፖፕ ከረሜላዎች፣ የምግብ ዘይት፣ ቪምቶ፣ የምግብ ጨው፣ የለውዝ ቅቤና የማር ምርቶች መሆናቸውም ተገልጿል።

ንጹህ የኑግ ዘይት፣ ኢዛና ዘይት፣ ጣና ዘይት፣ ኦሊያድ ዘይት፣ ስኬት የተጣራ ዘይት፣ በቅሳ የምግብ ዘይት፣ አሚን የምግብ ዘይት፣ ቀመር የምግብ ዘይት፣ ሎዛ የምግብ ዘይት፣ ዘመን የኑግ እና የለውዝ ዘይት፣ ዘቢብ ቃሀ የምግብ ዘይት፣ ማኢዳ የለውዝ ቅቤ፣ ሮዛ ክሬሚ ለውዝ ቅቤ፣ አዋሽ የገበታ ጨው፣ ሳራ እና ኑስራ ጨው።

ሴፍ የገበታ ጨው፣ ሽናጉ የገበታ ጨው፣ ወዛቴ አዮዳይዝድ ጨው፣ ቃና የገበታ ጨው፣ አስሊ የገበታ ጨው፣ ሲሳይ ንጹህ ማር እና ቅቤ፣ ወለላ ማር፣ ካርቶንስ ካንዲ ፍሩትስ፣ ሊዛ ሎሊ ፖፕ፣ ክሬሚ ሎሊ ፖፕ፣ ዳና ቪንቶ እና ቪንቶ ምርቶች በጥናት የተለዩ ናቸው።

በመሆኑም ህብረተሰቡ የትኛውንም የምግብ ምርት ከገበያ ሲገዛ የመጠቀሚያ የአገልግሎት ጊዜው ትክክለኛነት፣ የደረጃ ምልክት የለጠፈ፣ ያልተፋቀና ያልተሰረዘ መሆኑን እንዲሁም የአምራች ድርጅቱ ስምና ሙሉ አድራሻ፣ ያለው መሆኑን በማረጋገጥ መግዛት አለበት ተብሏል።

በተጨማሪም የምርት ገላጭ ጽሁፍ ይዘቶችን ያላሟላ ምርት ህብረተሰቡ ከመግዛት እንዲቆጠብ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አሳስቧል።

ተመሳሳይ ምርቶች በሌሎች አካባቢ የመገበያያ ስፍራዎች ሊኖር ስለሚችል ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ለሚገኝ የጤና ተቆጣጣሪ፣ ለፖሊስ አካላት ወይም በፌደራል ደረጃ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በነጻ የስልክ መስመር በ8482 በመጠቆም እንዲያሳውቅም ጠይቋል።

የክልል ተቆጣጣሪዎችና በየደረጃው የሚገኙ የቁጥጥር አካላት ምርቶቹን ከገበያ ላይ በአፋጣኝ የመሰብሰብ ስራውን እንዲሰሩ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጥሪ ማቅረቡን ከኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.