Fana: At a Speed of Life!

ዶክተር አዲሳለም ባሌማ ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህወሓት የጥፋት ቡድን ከፍተኛ አመራር የነበሩት ዶክተር አዲሳለም ባሌማ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ዶክተር አዲሳለም በፀረ-ሰላም ቡድን ተደራጅተው በመስራት ተጠርጥረው ፍረድ ቤት ቀርበዋል።

ተጠርጣሪው አምባሳደር በነበሩበት ዘመንም ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገራት ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት ለማበላሸት እና ለማስቆም ተፅዕኖ ሲፈጥሩና ሲሰሩ እንደነበር መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

በተጨማሪም የመንግስት መረጃና ሚስጥሮችን አሳልፈው ሲሰጡ እንደነበር መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አብራርቷል።

ከኦነግ ሸኔ ከፍተኛ አመራሮች ጋርም መረጃ ሲለዋወጡ እና የመንግስትን ሚስጥር አሳልፈው በመስጠት ለተፈፀሙ ወንጀሎች በጋራ ሲሰሩ እንደነበር አስረድቷል።

መርማሪ ፖሊስ ዶክተር አዲሳለም የአፍሪካ ከፍተኛ አመራሮች የፌዴራል መንግስት ላይ ጫና እንዲፈጥሩ ተፅዕኖ ሲያደርጉ እንደነበርና ህገ መንግስትንና ህገመንግስታዊ ስርዓትን ለመናድ ከዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና ከቡድናቸው ጋር በመሆን ወንጀል የሚፈፀምበትን ሁኔታና ዕቅድ ሲያወጡ እንደነበር ጠቅሷል።

በተጨማሪም ወጣቶችን በመመልመል ሁከትና አመፅ እንዲፈጠር በየክልሉ ሲያስተባሩ እንደነበር የጠቀሰው መርማሪ ፖሊስ፤ ዶክተር አዲሳለም ባሌማ ከቻይና አንድ አምባሳደር ጋር በመገናኘት የቻይና እና የህወሓት ኮሙኒስት ፓርቲ ለመፍጠር ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ሲሰሩ እንደነበረም ጠቅሷል።

ካልተያዙ ግብረአበሮቻቸው ጋርም በህዳር 24 ቀን፣ 2013 ዓ.ም በማይካድራ የንፁሀን ዜጎች እንዲጨፈጨፍ፣ የሰሜን እዝ ጦር ጥቃት እንዲፈፀምበትና ከባድ የጦር መሳያ እንዲዘረፍ ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ እንደነበር ለችሎቱ አስረድቷል።

መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት የጠየቀ ሲሆን፥ ተጠርጣሪው ከዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጋር በሽምግልና ጉዳይ ሰኞ ዕለት ስነጋገር ቆይቼ ረቡዕ በቁጥጥር ስር ውያለሁ፤ ሌሎች አምባሳደሮችንና ኃላፊዎችንም በሽምግልና ጉዳይ ነው ያነጋገርኳቸው ብለዋል።

ዶክተር አዲሳለም ወንጀሉን አልፈፀምኩም ያሉ ሲሆን፥ መርማሪ ፖሊስ ወንጀሉን ስለመፈፀማቸው የሚያስረዱ በቂ መረጃዎች እንዳሉት ለችሎቱ አብራርቷል።

ጉዳዩን የተከታተለው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎትም ለመርማሪ ፖሊስ 14 ተጨማሪ ቀናትን ፈቅዷል።

ታሪክ አዱኛ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.