Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ኮቫክስ ለተሰኘው ዓለም አቀፍ የክትባት ድጋፍ ሰጪ ተቋም የኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት ጥያቄ አቀረበች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ኢትዮጵያ ኮቫክስ ለተሰኘው ዓለም አቀፍ የክትባት ድጋፍ ሰጪ ተቋም የኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት ጥያቄ ማቅረቧን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
ወደ ምርመራ የገባው ባህላዊ መድሃኒት የመጀመሪያ ደረጃ የላብራቶሪ ምርመራ ማለፉም ተገልጿል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ “ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባትን ለማግኘት ጥረት እያደረገች ነው” ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ክትባቶች ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሱ መሆኑን ገልጸው÷ ኢትዮጵያም ክትባቱን እንድታገኝ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም ክትባቶችን በፍትሃዊነት ለማሠራጨት ከሚሰራው ‘ኮቫክስ’ ከተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም ጋር ክትባቱን በፍጥነት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዚህም ደግሞ የጤና ሚኒስቴር የሚመራው ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ክትባቱን ለማግኘት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን የሟማላት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ክትባቱን ለማግኘት በግብረ ኃይሉ የተሠራው ዝርዝር እቅድ ለተቋሙ መላኩን ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙሉ በሙሉ ማኅበረሰቡን የመከተብ ሁኔታ አለመኖሩን የጠቀሱት ሚኒስትሯ በኢትዮጵያም ለተወሰኑ ሠዎች በቅድሚያ የሚዳረስ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ዓለም አቀፍና ብሔራዊ አሰራሮችን በመከተል የሚከናወን መሆኑን ጠቅሰው÷ ለተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች ቅድሚያ ለመሥጠት መታቀዱን ጠቁመዋል።
ክትባቱን በስፋት ለማስገባት የሚያስፈልገውን ተጨማሪ የፋይናንስ ፍላጎትን የዓለም ባንክ ድጋፍ እንዲያደርግ ከተቋሙ ጋር እየተወያዩ መሆኑን አስረድተዋል።
ጎን ለጎንም ወደ ምርመራ የገባው ባህላዊ መድሃኒት የመጀመሪያ ደረጃ የላብራቶሪ ምርመራ በማለፍ ሁለተኛ ደረጃ የላብራቶሪ ምርመራ ላይ መድረሱን አስታውሰዋል።
መድሃኒቱ አሁን ባለበት የምርመራ ደረጃ ከውጭ ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ ከውጤት በኋላ መድሃኒቱ ወደ ክሊኒካል ምርመራ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በትግራይ ክልል የኮቪድ-19 ምርመራን ጨምሮ ሌሎች የጤና አገልግሎቶች እንዳይስተጓጎሉ ለማድረግ ከሠላም ሚኒስቴር ጋር እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል
https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.