ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ለ532 የፀረ-ሽብር ግብር ሃይል ባለሙያዎች ስልጠና ሰጠ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2012(ኤፍቢሲ) የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ከሀገሪቱ የፀጥታና የመረጃ ተቋማት ለተወጣጡ 532 የፀረ-ሽብር ግብር ሃይል ባለሙያዎች ሽብርተኝነትን የመከላከል እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ሥልጠና መሥጠቱን አስታውቋል።
አገልግሎቱ ከመከላከያ፣ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ለተወጣጡ የፀረ-ሽብር ግብር ሃይል ባለሙያዎች ነው ስልጠና የሰጠው፡፡
ስልጠናው በአሁኑ ወቅት በዓለምአቀፍ ደረጃ እና በአፍሪካ ቀንድ እየተስፋፋ የመጣውን የሽብርተኝነት እንቅስቃሴን፣ስልትና ስጋትን፣የመከላከል ዘዴዎችን እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።
በቅርቡ በአፍሪካ ቀንድና በመካከለኛው አፍሪካ አልሸባብ፣አልቃይዳና አይኤስ በተባሉ የሽብር ቡድኖች አማካኝነት የደረሱ የሽብር ጥቃቶች በኢትዮጵያም እንዳይከሰቱ የፀጥታ አካላት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና የሽብር ጥቃቶችን የመከላከል አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ሥልጠናው እገዛ እንደሚኖረው ተመልክቷል።
እንዲሁም ስልጠናው በቅርቡ የሚከበሩት የገናና የጥምቀት በዓላትን ጨምሮ የዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት እንዲሁም የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄዱ የፀጥታና የመረጃ ተቋማት ቅድም ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑ ተገልፆል፡፡
ህብረተሰቡም ፀጥታን ሊያውኩ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች ሲመለከት፤ በአቅራቢያው ለሚገኙ የፀጥታና የመረጃ ተቋማት አስፈላጊውን ጥቆማ እንዲሰጥ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጥሪ አቅርቧል።