Fana: At a Speed of Life!

ለድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የህይወት ኢንሹራንስ ሊገባላቸው መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ለድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የህይወት ኢንሹራንስ ሊገባላቸው መሆኑ ትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው በጉዳዩ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር  ውይይት ከተካሄደ በኋላ መግባባት በመደረሱ ነው ተብሏል፡፡

በጥቂት ሣምንታት ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው የህይወት ኢንሹራንሱ በባለንብረቶችና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሚከፈል የአረቦን መጠን የሚሸፈን መሆኑ ተጠቁሟል።

በመሆኑም አሽከርካሪዎቹና ረዳቶቻቸው በኮሮና ህይወታቸው ሲያልፍ ለአሽከርካሪዎቹ ቤተሰብ 250 ሺህ ብር ለረዳት ቤተሰብ ደግሞ 150 ሺህ ብር ካሳ ያገኛሉ ተብሏል፡፡

በሚኒስትር ዲኤታ ማዕረግ የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩና በፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ በተመራው መድረክ ላይ እንደተገለጸው ስምንት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ስራውን አስቀድመው ለመጀመር ቅድመ-ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸው ነው የተገለጸው፡፡

የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ የኢንሹራንስ ሰርተፊኬቱን ህትመት እንደጨረሰ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በመድረኩ ላይ የመድን ሰጪዎችና የድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ማህበራት እንዲሁም የድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ማህበራት ፌዴሬሽን ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

አገልግሎቱን በማስተባበርና ክትትልና ድጋፍ በማድረግ በኩል የትራንስፖርት ባለስልጣንና የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ በጋራ እንደሚሰሩ ነው የተጠቀሰው፡፡

ኢንሹራንሱ ለአንድ ዓመት የሚያገለግል ሆኖ እንዳስፈላጊነቱ በየዓመቱ ይታደሳል መባሉን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.