Fana: At a Speed of Life!

ከስደት ተመላሽ ዜጎችን ወደ ስራ ማስገባት ላይ ያለውን የቅንጅት ክፍተት መፍታት ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከስደት ተመላሽ ዜጎችን ወደ ስራ ማስገባት ላይ ያለውን የቅንጅት ክፍተት መፍታት እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
 
ከስደት ተመላሽ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም ላይ የተከናወኑ ተግባራት ቢሮሩም አሁን ድረስ አመርቂ ውጤት አለመመዝገቡ ይነገራል ፡፡
 
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ከስደት ተመላሽ ዜጎች በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት ጠንካራ ስራዎች ይጠበቃሉ ብለዋል ፡፡
 
የአማራ እና ደቡብ ክልል የስራ እድል ፈጠራ ቢሮዎች በበኩላቸዉ ÷ ከዚህ ቀደም የተወሰዱ ብድሮች በወቅቱ አለመመለሳቸው እነዚህን ዜጎች በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት እንቅፋት እንደሆነባው ያነሳሉ ፡፡
 
የአማራ ክልል የቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የስራ እድል ፈጠራ ዳይሬክተር አቶ ስላባት ሰውአገኝ ÷ ብድርን በወቅቱ ካለመመለስ ባሻገር ተመላሾችን ለማቋቋም የሚሰሩ ስራዎች በተቀናጀ መልኩ አለመከናወናቸው የሚፈለገው ውጤት እንዳይመዘገብ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
 
የደቡብ ክልል ኢንተርፕራይዞች እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አማን ኑረዲንም በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
 
 
በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ሃገር ስራ ስምሪት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አበራ ÷ ዘርፉ በሚፈለገዉ መልኩ በባለቤትነት አለመመራቱ እና ቅንጅታዊ አሰራሮች ክፍተት የሚጠበቀው ውጤት እንዳይመጣ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
 
በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን ለመፍታት ከመቸውም ጊዜ በላይ የጋራ ስራዎች እንደሚጠበቁም ጠቁመዋል ፡፡
 
 
 
በአወል አበራ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.