Fana: At a Speed of Life!

ባለስልጣኑ 14 ኪሎ ሜትር የኮብል ስቶን ንጣፍ እና የአስፋልት ጥገና ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 2፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ውስጥ በከተማችን የተለያዩ አካባቢዎች 14 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን የኮብል ስቶን መንገድ ንጣፍ ማከናወኑን እና የአስፋልት ጥገና ስራዎችን ደግሞ እያከናወነ እንድሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በበጀት አመቱ 150 ኪሎ ሜትር የኮብል ስቶን ንጣፍና ጥገና ስራ ለማከናወን እቅድ ይዞ ወደ ስራ የገባ ሲሆን ባለፉት አምስት ወራትም 25 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮብል ስቶን መንገዶችን ለመገንባትና ለመጠገን አቅዶ 14 ኪሎ ሜትር የሚሆነውን ብቻ ማከናወኑ ተጠቁሟል፡፡

የኮብል ስቶን ንጣፍ ስራ በታቀደው እቅድ መሰረት እንዲከናወን ለማድረግ የሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የኮብል ስቶን ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ብስራተ ገብርኤል አሰፋ አሳስበዋል፡፡

የውስጥ ለውስጥ የኮብል ስቶን ንጣፍ ስራው በአስሩም ክፍለ ከተማ እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት ኢንጅነር ብስራተ ገብርኤል አሁን ላይ የኮብል ስቶን ንጣፍ ስራ ለማከናወን የሚደረገው የቅድመ ዝግጅት ስራ በሌላ ተቋም የሚከናወን በመሆኑ ስራው በሚፈለገው ፍጥነትና በተያዘው እቅድ መሰረት ለማከናወን ተፅእኖ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በአምስት ወራት ውስጥ ከተያዘው እቅድ አኳያ የእቅዱን 54 በመቶ ያህሉን ብቻ ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በቀጣይም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የኮብል ስቶን ንጣፍ ስራውን ከሰብ ቤዝ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ኮብል ስቶን ማንጠፍ ድረስ ያለውን ሂደት በባለቤትነት እንዲያከናውን የሚል አቅጣጫ መቀመጡን ኢንጂነሩ  ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በልዩ ልዩ ምክንያቶች ለጉዳት በመዳረጋቸው የትራፊክ እንቅስቃሴን የሚያውኩ ዋና ዋና እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በመለየት የአስፋልት ጥገና ስራ ባለስልጣኑ በማከነወን ላይ ነው፡፡

ባለስልጣኑ የተለያዩ የመንገድ ጥገና ስራዎች እያከናወነባቸው ከሚገኙ አካባቢዎች መካከል ከፖርላማ እሪ በከንቱ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ – ፖርላማ መብራት፣ ካዲስኮ መብራት አካባቢ፣ ከጐርጐሪዮስ አደባባይ – ሚካኤል፣ ከተክለሀይማኖት አደባባይ – ሲኒማ ራስ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከአስፋልት ጥገና ስራ ጐን ለጐን የድሬኔጅ መስመር ጥገና እና ግንባታ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

የድሬኔጅ ጥገና ስራ እየተከናወነባቸው ከሚገኙ አካባቢዎች መካከል ከተክለኃይማኖት – ሱማሌ ተራ፣ ከጃል ሜዳ – ሚሊኒክ ሆስፒታል፣ ከጦርኃይሎች – ቶታል፣ ወይራ ኮቪድ 19 ማዕከል አካባቢ፣ ከፖስተር – አለምፀሀይ ድልድይ፣ ከአዲሱ ገበያ – እግዚአብሄር አብ፣ ጀርመን አደባባይ፣ ጃፖን ኤምባሲ አካባቢ፣ ከማሰልጠኛ – ካዲስኮ፣ ከሲ.ኤም.ሲ – ሰሚት፣ አምቼ – እግዚአብሄር አብ እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.