የሀገር ውስጥ ዜና

ሀገርን እና ወገንን ማገልገል የዘወትር መልካም ባህል ሊሆን ይገባል- የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

By Meseret Awoke

December 12, 2020

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀገርን እና ወገንን ማገልገል የዘወትር መልካም ባህል እንዲሆን የኦሮሚያ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ጥሪ አቀረቡ።

የዜግነት አገልግሎት ወቅትን ጠብቆ የሚካሄድ ባለመሆኑ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜና ስፍራ ሁሉ በጋራ መቆም፣ መስራት፣ መደጋገፍና መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ባለፈው ክረምት ችግኞችን ስንተክል በጋራ እንደሰራነው ሁሉ በመንከባከቡም ግዴታችንን እንወጣ ብለዋል።

አረጋውያንን እና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ፣ በተለያዩ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸውን በመርዳት፣ አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸውም እጃችንን እንዘርጋ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ሀገርን እና ወገንን ማገልገል እንዲሁም የበጎ አድራጎት ስራ በገዳ ስርዓት እና በኦሮሞ ባህል ታላቅ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

አቶ ሽመልስ እስካሁን የተሳተፉትን ሁሉ አመስግነው በቀጣይም ወቅትን ሳንጠብቅ አገልግሎቱን ባህል በማድረግ ሀገርንና ወገንን እናገልግል ብለዋል።