Fana: At a Speed of Life!

ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች በከተማው የሚገኙ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በከተማው የሚገኙ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጎበኙ፡፡

በምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ የተመራው የከተማዋ አመራር ልዑክ በአዲስ አበባ የሚገኙ የቂሊንጦ ፋርማሲዩቲካ፣ የአይ.ሲ.ቲ እንዲሁም የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርኮችን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሀላፊዎችም ተገኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ አጠቃላይ በፓርኮቹ የተከናወኑ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የምርት ሂደት፣የስራ ዕድል ፈጠራ፣በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ፣የኢንደስትሪው ሰራተኞች ሁኔታ ፣የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ጉዳይ ፣ የአካባቢ እንክብካቤና ወሰን ማስከበርን በተመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ለተነሱ ጥያቄዎች የኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ለልማት ተነሺ አርሶአደሮች የተለያዩ የስራ ዕድሎችን ለመፍጠርና ለአካባቢው ነዋሪም የሚያግዙ የልማት ተግባራት ላይ እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በዚህም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመቀናጀት ስራዎችን እየሰሩ እንዳሉ በማብራራት ከከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት የተጀመረው አጠቃላይ እድገት የተሳካ እንዲሆን ማህበረሰቡን ታሳቢ ማድረግ እንዳለበት ገልጸው መሠረተ ልማት እና በሌሎች ምክንያቶች ከመኖሪያና ከስራ ቦታቸው የተነሱ አርሶ አደሮች፣ ስራ ፈላጊ ወጣቶች፣ በኢንደስትሪው ውስጥ በሰራተኝነትና በዙሪያው ባለ አካባቢ ደግሞ በነዋሪነት የሚገኙ ሴቶች ተጠቃሚነትን በተመለከተ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።

በኢንደስትሪ ፓርኮቹ በኩል ለቀረበው የድጋፍ ጥያቄም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በየጊዜው ስራው የደረሰበትን ደረጃ እየታየ በጠንካራ የስራ ትስስር እንዲመራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.