Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና መሰል በሽታዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የምርምር ተቋማት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና መሰል በሽታዎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ የምርምር ተቋማት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡

በጤና ዘርፍ የሚካሄዱ ምርምሮችን ውጤታማ ለማድረግ አውደጥናት ተካሂዷል፡፡

አውደ ጥናቱን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከብሔራዊ የእንስሳት ምርምርና ጥናት ማዕከል ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል፡፡

በመድረኩም የጤና ጥበቃ እና የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታዎች እንዲሁም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር እና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

አውደ ጥናቱ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ለመሰል በሽታዎች ህክምና የሚሆኑ የባህል መድሃኒቶችን ለማግኘትና ለመጠቀም በትብብር እና በቅንጅት ጥናት ለማካሄድና አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚረዳ ነው ተብሏል፡፡

በሰበታ ከተማ በብሄራዊ የእንሰሳትና ምርምር እና ጥናት ማዕከል በተካሄደው አውደጥናት ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ለረጅም አመታት አባቶቻችን ለሰውና ለእንሰሳት ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን የባህል መድሃኒቶች በዘመናዊ መልክ የመለወጡ ጉዳይ ክፍተት ያለው መሆኑን አንስተዋል፡፡

አጠቃላይ ስለኮሮና ቫይረስ ያለው እውቀት አነስተኛ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ደረጄ በባህል መድሃነት ህክምና ላይ የተጀመሩ ስራዎች ቢኖሩም በቀጣይ በቅንጅት ውጤታማ የምርምር ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በበኩላቸው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ከመቆጣጠር አንጻር፣ የላቦራቶሪ አቅምን ከመገንባት እና የተለያዩ ጥናትና ምርመሮችን ከማድረግ አንጻር የምርምር ተቋማት መዋቅራዊ በሆነ መንገድ በቅንጅትና በጋራ

የሚሰሩ ከሆነ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ አንስተዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ እና የብሄራዊ የእንሰሳት ምርምርና ጥናት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ ሩፋኤል በተመሳሳይ መልኩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና የምርምር ማዕከሉ እየሰሯቸው ስላሉት የምርምር ስራዎች እንዲሁም አጠቃላይ የምክክር መድረኩን አላማ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ስዎችን ከፍተኛ ህመም በማስታገስና ቶሎ እንዲድኑ የሚያግዙ ከባህል መድሃኒት በዘመናዊ መልክ የተቀመሙትንና በተለያዩ የምርምር ዩኒቫርሲቲዎች ጥናት እየተደረገባቸው ያሉትን የባህል መድሃኒቶች በቀጣይ ስለሚደረገው የምርምር ሂደት ሰፊ ውይይት በማድረግ አቅጣጫዎች ተቀምጧል፡፡

ዘርፈ ብዙ የምርምር ተቋማትና የተለያዩ ባለሙያዎች፣ በባህል ህክምና ምርምር የተሰማሩ ተመራማሪዎች እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን በአውደ ጥናቱ ላይ መሳተፋቸውን ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.