የብልፅግና ፓርቲ የሚሰራው ለትውልድ እንጂ ለምርጫ አይደለም- ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የሚሰራው ለትውልድ እንጂ ለምርጫ አይደለም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ።
በአዲስ አበባ ከተማ በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራምና ህገ ደንብ ዙሪያ “በህብር ወደ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል የግንዛቤ ሲካሄዱ የነበሩ ማስጨበጫ መድረኮች ማጠቃለያ ተካሂዷል።
በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም ከ10 ሺህ በላይ የከተማዋ ወጣቶች ታድመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በመድረኩ ባስተላለፉት መልእክት፥ “የብልፅግና አስተሳሰብን እና አሰራርን በቀጣይ 50 እና 60 ዓመታት ማሸነፍ ከባድ ነው፤ ማንም እኔን ቢያሸንፍ ከብልፅግና ሀሳብ ወዲያ ግን ኢትዮጵያን ለወራትም ቢሆን ማስተዳድር ይከብደዋል” ብለዋል።
“ብልፅግናን በመክሰስ ሳይሆን፤ ከብልፅግና በመማር እና የብልፅግና እሳቤዎችን በማሻሻል ብቻ ነው ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራው” ሲሉም ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አክለውም፥ ወጣቶች በምርጫ ወቅቶች ለተወዳዳሪዎች ድምፃቸውን እንጂ ህይወታቸውን መገበር አይገባቸውም ሲሉም ተናግረዋል።
ወጣቶች ህልማቸውን ሊነጥቁ ከተዘጋጁ ጉዳዮች በመራቅ የብልጽግና ጎዳናን መከተል ይገባቸዋልም ብለዋል።
ሰውን አጋድሎ እና አጣልቶ ስልጣን ለመያዝ ያለመ ካለ አስተሳሰቡ ራሱ የቆሸሸ ነው እና ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፤ ስለዚህ ወጣቶች መንቃት ይኖርባችዋል ብለዋል።
በሚከሰቱ ግጭቶች ወጣቶች እየተጎዱ ነው፤ ወጣቱን ተገፋፍቶ ወዳልተፈለገ ነገር የሚያስገቡ ሀይሎች ሲሞቱ አስይስተዋልም፤ ወጣት ስለሆናችሁ ለማናችንም ቢሆን ካርዳችሁን እንጂ ህይወታችሁን አትስጡ ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ብልፅግናን ከወደዳችሁ ድምጽ ስጡት፤ ካልወደዳችሁት ግን በድምጽ ቅጡት ለማንም ቢሆን ህይወታችሁን አትስጡም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
“በህብር ወደ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራምና ህገ ደንብ ዙሪያ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት እና የምክክር መድረኮች ሲካሄዱ መቆየታቸው ይታወሳል።
የውይይት እና የምክክር መድረኮቹ በሁሉም ክፍለ ከተማ ከተሞችና ወረዳዎች ላይ የተካሄዱ ሲሆን፥ በመድረኮቹም የመደመር ጽንሰ ሀሳብ እና የብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራምና ህገ ደንብ ላይ ሰፊ ውይይቶች ተደርግዋል።
የኢህአዴግ ውህደት ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርአት ከመገንባት አኳያ ውህደቱ ሁሉን አካታች መሆኑ እና የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳ ዘንድ ውህደቱ አስፈላጊ መሆኑ የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ ውይይት መድረኮች እንደተገለጸው ብልጽግና ፓርቲ ህዝባዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነት፣ የህግ የበላይነት፣ ሀገራዊ አንድነት እና ህብረ ብሄራዊነት መርሆችን የሚከተል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ የህዝቦች ክብር፣ ፍትህና ህብረ ብሄራዊ አንድነት እውነተኛ የፌደራሊዝም ሥርዓት እውን የሚሆንበት ነው ተብሏል።
ብልጽግና ፓርቲ በፕሮግራሙ ጠንካራና ተቀባይነት ያለው ዘላቂ መንግሥታዊ መዋቅርና ተቋማት መገንባት፣ የብሔር ማንነትና ሀገራዊ አንድነት ሚዛን የጠበቀ ማድረግ እንዲሁም አንድ ጠንካራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠር አላማ እንዳለው በውይይት መድረኮቹ ተነስቷል።