Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ሙሉ ለሙሉ ወደነበረበት ለመመለስ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ወደነበረበት ለመመለስ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የመካከለኛና የዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችን ለመጠገንና ተቋርጦ የነበረውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ወደነበረበት ለመመለስ የቴክኒክ ባለሙያዎችን በመላክ ሰፊ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልጿል፡፡

የቴክኒክ ባለሙያዎቹ ከትግራይ ክልል እና ከአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተውጣጡ መሆናቸውን ድርጅቱ ጠቅሷል፡፡

በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ የተሰማራው ግብረ ሃይል እስካሁን ወልቃይት፣ ሁመራ፣ ማይካድራ፣ አብድራፊ፣ አብረሃጅራ፣ ባዕከር፣ አዲረመጥና አዲጎሹ ከተሞች ላይ ያለው የዝቅተኛና መካከለኛ መስመር ጥገና ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጉም ተገልጿል፡፡

ከባዕከር እስከ አዲረመጥ እና ከባዕከር እስከ ዳንሻ እንዲሁም ከማይፀብሪ እስከ አድርቃይ ያለው የመካከለኛና የዝቅተኛ ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ጥገናም ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ከሽረ እስከ ማይፀብሪ ከተሞች ያለውን መስመር ጥገና ሥራም ለማከናወን ጥረት እያደረገ ይገኛልም ነው ያለው፡፡

በደቡባዊ አቅጣጫ ደግሞ ራያ ቆቦ፣ ጥሙጋ፣ ዋጃ፣ አላማጣ፣ ኮረም፣ ማይጨው፣ መኾኒ እንዲሁም ከአላማጣ ንዑስ ጣቢያ ኃይል የሚያገኙትን ላሊበላና ሰቆጣ ከተሞች ላይ የደረሰውን ጉዳት ጠግኖ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ አድርጓልም ብሏል፡፡

በትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋቋመው የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን ደግሞ የመቐለ ከተማን ጨምሮ በኩዊሀ እና በአዲጉዶም ከተሞች ያለውን የዝቅተኛና መካከለኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር በመጠገን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉ የሚታወቅ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የውቅሮና የአዲግራት ከተሞች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ እየተሰራ ሲሆን፤ በቀጣይም በአክሱም እና በሽረ ከተሞች ያለውን የዝቅተኛና መካከለኛ ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ለመጠገን አስፈላጊ ዝግጅት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

በቀጣይም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማቶች ጠግኖ ሁሉንም የክልሉ ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ አሁን ከተሰማራው ኃይል በተጨማሪ የተቋሙ ከፍተኛ ማኔጅመንት አባላት እንዲሁም ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተውጣጡ የቴክኒክ ባለሙያዎችን የያዘ ግብረ ኃይል በፍጥነት ወደ ሥፍራው እንደሚልክም አስታውቋል፡፡

ግብረሃይሉ በትግራይ ክልል ያሉትን የጥገና ባለሙያዎች የሚያግዝ፣ የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያስፈልገውን አስፈላጊ ድጋፎች በመለየት የሚያቀርብና በአጭር ጊዜ ውስጥ ህብረተሰቡ የሚፈልገውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማቅረብ እንዲቻል ሁኔታዎችን የሚያመቻች እንደሆነም ነው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.