Fana: At a Speed of Life!

የሙለር ሪልስቴት ባለቤት እና ብርጋዴር ጄኔራል አብርሃም ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሙለር ሪል ስቴት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ እና ብርጋዴር ጄኔራል አብርሃም መውጫ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

በእነ ሙለር ሪል ስቴት ባለቤት መዝገብ የተካተተ ተጠርጣሪም ከ81 ሚሊየን ብር በላይ በአንበሳ ባንክ በኩል ለጽንፈኛው የህውሓት ቡድን ድጋፍ ለማድረግ ሲያዘዋውር እንደነበር መረጃ ማግኘቱን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ ለመሬት በሚል በማህበር ተደራጅተው ከአንበሳ ባንክ በተጨማሪ በአራት ባንኮች ለፀረ ሰላም ቡድኑ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ እንደነበር ነው የተገለጸው።

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምደብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት አራት መዝገቦቸን ተመልክቷል።

በቀዳሚነት መዝገብ የቀረቡት ብርጋዴር ጄኔራል አብርሃም መውጫን ጨምሮ አምስት መኮንኖች የተመለከተው ችሎቱ÷ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ አባል ከዚህ በፊት በተሰጠው 12 ቀናት ውስጥ የሰራውን የምርመራ ስራ ለፍርድ ቤቱ አብራርቷል።

በዚህም በርካታ የምርመራ ስራ ማከናወኑን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ የተናጠል ተሳትፎዋቸውን መለየቱን ገልጿል።

በዚህ ተሳትፎ ተጠርጣሪዎቹ ከጸረ ሰላም ሃይሎች ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት በማድረግ በጋራ በመደራጀት ለሰሜን ዕዝ ጥቃት መፈጸም ሲሰሩ እንደነበር በቴክኒክና በሰበሰብኩት የሰው ማስረጃ ማረጋገጥ ችያለሁ ሲል አብራርቷል።

ተጠርጣሪዎቹ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው በማስረዳት ለፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄም አንስተዋል።

የባንክ ሂሳባቸው በመታገዱ ለቤተሰብ ቀለብ መቸገራቸውን አቤቱታ አቀርበዋል።

የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ ፖሊስ በርካታ ምርመራ ማድረጉን የሚያመላክቱ ማስረጃዎች መሰብሰባቸውን ገልጾ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ተጨማሪ ቀናት ፈቅዷል።

በሁለተኛ መዝገብ የቀረቡት በእነ ሙለር ሪል ስቴት ባለቤት ሙሉጌታ ተስፋኪሮስን ጨምሮ አራት ተጠርጣሪዎች ጉዳይም ታይቷል።

ተጠርጣሪዎቹ ሃይሌ መዝገቡ፣ ሃየሎም ዘራብሩክ፣ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ እና ሳሙኤል አባዲ ናቸው።

መርማሪ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሰራውን በርካታ የምርመራ ስራ ለችሎቱ ይፋ አድርጓል።

በዚህም ምርመራ ተጠርጣሪዎቹ ለህወሓት ጸረ ሰላም ቡድን ድጋፍ የሚውል ከአራት ባንኮች በርካታ ብር ያስገቡበትን ማስረጃ አግኝቻለሁ ብሏል ፖሊስ።

በተለይም 1ኛ ተጠርጣሪ ሃይሌ መዝገቡ ከአንበሳ ባንክ ከ81 ሚሊየን ብር በላይ ለቡድኑ የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቡን በማስረጃ ማረጋገጡን ነው የገለጸው፡፡

መርማሪ ፖሊስ÷ 2ኛ ተጠርጣሪ ሀየሎም ዘራብሩክ ላይ ባደረኩት ምርመራ በርካታ የባንክ ሂሳብን በመጠቀም ለጸረ ሰላም ቡድኑ ለወንጀል መፈጸሚያ ድጋፍ ማድረጉን በማስረጃ ማሰባሰቡን ለችሎቱ አስረድቷል።

3ኛ ተጠርጣሪ የሙለር ሪል እስቴት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ በርካታ ብሮች በማሰባሰብ ወንጀሉ እንዲፈጸም የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን አረጋገጫለሁ ያለው መርማሪ ፖሊስ 4ኛ ተጠርጣሪ ሳሙኤል አባዲን በተመለከተም መርማሪ ፖሊስ ከእርሳቸው የህወሓት ጸረ ሰላም ቡድን ዝርዝር የያዘ በሰንጠረዥ የተሰራ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝርዝር ማስረጃ ማግኘቱንም ገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት የለንም ያሉ ሲሆን÷ 4ኛ ተጠርጣሪም በፍላሽ የተገኘው የማህበር ነው በባንክም ገቢ የተሰበሰበው የማህበር ብር ነው ያሉ ሲሆን መርማሪ ፖሊስ ግን ብሩ በመሬት በሚል በማህበር ተደራጅተው ህጋዊ ሽፋን በመስጠት ብር በማሰባሰብ ለትግራይ ልዩ ሃይል ለወንጀል መፈጸሚያ የተሰባሰበ ነው ብሏል በምላሹ።

የሙለር ሪልስቴት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ጠበቃ በበኩላቸው በተሰጠው የምርመራ ጊዜ መጠናቀቅ ያለባቸው ጉዳዮች በድጋሚ ቀርበው ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ አግባብ አይደለም በሚል የደንበኛቸው የባንክ ሂሳብ በ30 ደቂቃ ማጣራት ይቻላል ተጨማሪ ጊዜ አያስጠይቅም ሲሉ ተቃውመዋል።

አቶ ሙሉጌታም በራሳቸው ከ1ሺህ በላይ ሰራተኞች እንዳላቸው ገልጸው ቤታቸው ሲመጡ ካሜራና ስልኬን ለመመርመራ መስጠታቸውን በመጥቀስ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉት ለሸገር ልማት እንጂ ለሌላ አይደለም በማለት ፍርድ ቤቱ ዋስትናቸውን እንዲያስጠብቅ ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስም ዛሬ የገለጸው በተሰጠው ጊዜ የሰራውን መሆኑን በመጥቀስ ግለሰቦቹ በህገወጥ መንገድ ተደራጅተው ህጋዊ አስመስለው ለጸረሰላም ሃይሉ በርካታ ብር ሲያሰባስቡ እንደነበር አስረድቷል።

ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱም ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ በርካታ ማስረጃዎችን የሰበሰበ ቢሆንም ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ያስፈልገዋል ሲል የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዶለታል።

 

በታሪክ አዱኛ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.