Fana: At a Speed of Life!

በሀገሪቱ እድገት ውስጥ የግንባታ ዘርፉን ሚና ለማሳደግ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስት የግንባታው ዘርፍ በቀጣይ 10 ዓመታት የሀገሪቱ እድገት ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ።

ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የንቅናቄ መድረክ “ተወዳዳሪ ሀገር በቀል የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለኢትዮጵያ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የግንባታው ዘፍር ለአንድ ሃገር እድገት መሰረት ከሆኑት መካከል አንደኛው መሆኑን ተናግረዋል።

የግንባታው ዘርፍ ለሙስና እና ለስርቆት የተጋለጠ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከስርቆት ነጻ የሆነ የግንባታ ዘርፍ ሳይኖር ብልፅግና ጋር መድረስ አዳጋች መሆኑን አስረድተዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችም ከስርቆትና ከሙስና በፀዳ መልኩና በጥራት ለሀገር ዕድገት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስሩ አክለውም፥ በቀጣይ 10 ዓመታት የግንባታው ዘርፍ በሀገሪቱ እድገት ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተዘጋጀውና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚቃኘው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ንቅናቄ መድረክ እስከ ነገ የሚቀጥል ይሆናል።

የንቅናቄ መድረኩ ዓላማ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በግንባታው ኢንዱስትሪ የሚስተዋሉ ወቅታዊ ተግዳሮቶች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ ግንዛቤና መግባባት በመፍጠር ለኢንዱስትሪው አጠቃላይ ዕድገት የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ ነው።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.