Fana: At a Speed of Life!

የአውራምባ ታይምስ ባለቤትና ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ በተጠረጠረበት ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርቦ ተከራከረ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የአውራምባ ታይምስ ባለቤትና ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ባህታ በተጠረጠረበት ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርቦ ተከራክሯል፡፡

ተጠርጣሪው ላይ መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው 13 ቀናት ጊዜ የሰራውን የምርመራ ስራ ለችሎቱ አብራርቷል።

የተለያዩ መልካም ጎን ያላቸው የመንግስት ፕሮግራሞችን በመጥፎ ጎን በመተርጎም ለትግራይ ቲቪ እና ድምጸ ወያኔ ቴሌቪዥን መረጃ ሲልክ እንደነበር ባገኘሁት ማስረጃ አረጋግጫለሁ ነው ያለው ፖሊስ።

በማህበራዊ ድረገጽ ግጭት ሲቀሰቅስ እንደነበር በማስረጃ አረጋግጫለሁ ያለው መርማሪ ፖሊስ፥ በፌደራል መንግስት ላይ ጫና እንዲፈጠር በተለያየ ጊዜ ቅስቀሳ ሲያደርግ ነበርም ነው ያለው ለችሎቱ ።

የጦር መሳሪያ ከትግራይ ከልል መውጣት የለበትም፣ በእናቶቻቸን እና አባቶቻችን ደም የመጣ የጦር መሳሪያ ነው በማለት የትግራይ ወጣቶች መንገድ እንዲዘጉ እና የጦር መሳሪያውን እንዳያስወጡ ቅስቀሳ ሲያደርግ እንደነበር ባገኘሁት ማስረጃ አረጋግጫለሁም ብሏል።

መርማሪ ፖሊስ ከተጠርጣሪው ጋር ሲሰሩ የነበሩ የድምጸ ወያኔና የትግራይ ቲቪ ግብረ አበሮቹን ጨምሮ ለመያዝ በክትትል ላይ እንደሚገኝ ገልጾ፣ ከጀመርኩት ሰፊ የምርመራ ስራ አንጻር ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል ሲል ችሎቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቃ ተጠርጣሪው የፖለቲካ የምርመራ ጋዜጠኛ መሆኑን በመጥቀስ፤ በሚሰራቸው ቃለመጠይቆች መረጃዎችን በራሱ ድረገጽ እንደሚለጥፍ የተናገረ ሲሆን፤ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት የለውም፤ በሚሰራው የምርመራ ጋዜጠኝነትም ሊጠየቅ አይገባም ብሏል፡፡

ሃሰተኛ ዜና በመስራትም ቢሆን ከስድስት ወር ባልበለጠ ነው ቅጣት የሚጣልበት ሲል በዋስ ወጥቶ ጉዳዩን በውጭ እንዲከታተልም ጠይቋል።

ተጠርጣሪ ዳዊት ከበደ በበኩሉ ‘‘እኔ በራሴ ድረገጽ ነው የምሰራው የተለየ ቅስቀሳ አልሰራሁም፤ የህወሓት አመራሮችን ቃለመጠየቅ ስለሰራሁ ነው እንደወንጀለኛ በየሚዲያው እየተዘገበ ያለው’’ ሲል ተከራክሯል።

መርማሪ ፖሊስም ከሰኔ ወር ጀምሮ ዳዊት ከበደ ከአውራምባ በተጨማሪ ህገወጥ መረጃ ከሚያስተላለፉ እና መያዣ ከወጣባቸው የትግራይ እና የደምጸ ወያኔ ጋዜጠኞች ጋር ሃሰተኛ እና ብጥብጥ የሚፈጥሩ መረጃ ሲያስተላልፍ እንደነበር አንስቷል።

ስለሆነም ተጠርጣሪው በዋስ ቢወጣ ማስረጃ ሊያሸሽና የምርመራ ስራ ሊያደናቅፍ ይችላል ሲል መርማሪ ፖሊስ ዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል።

መዝገቡን የመረመረው ችሎቱ ለመርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ 10 ቀናት ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.