Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ባለፈው አንድ ወር ከ2 ሺህ 700 በላይ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች መያዛቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ባለፈው አንድ ወር ከ2 ሺህ 700 በላይ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች መያዙን አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከፌደራል ፖሊስና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ መኖሪያ ቤቶች፣ ተቋማት እና ተሽከርካሪዎች ላይ ህግን ለማስከበር ባደረገው ብርበራ እና ፍተሻ የጦር መሳሪያዎቹን ጨምሮ ከ80 ሺህ በላይ ልዩ ልዩ ጥይቶች መያዙን አስታውቋል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ በከሃዲው የህወሓት ቡድን የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት ህግን የማስከበር ዘመቻ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የጁንታውን ቡድን ተልዕኮ ተቀብለው በአዲስ አበባ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም እና በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ሃይሎች ዕቅዳቸው እንዳይሳካ ለማድረግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከፌደራል ፖሊስ፣ ከሌሎች የፀጥታ አካላት እና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀው፡፡
ኮሚሽኑ ከጥቅምት 25 ቀን እስከ ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም ባለው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በህዝብ ጥቆማ እና በፀጥታ አካላት በተጠረጠሩ መኖሪያ ቤቶች እና ልዩ ልዩ ተቋማት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ባደረገው ብርበራ እንዲሁም በተሽከርካሪዎች ላይ በተከናወነ ፍተሻ 60 የእጅ ቦምብ፣ 1 ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂ፣ ከ141 በላይ የእጅ እና የጦር ሜዳ የረጅም ርቀት የትከሻ የሬዲዮ መገናኛ፣ 809 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ 2 ላውንቸር፣ 976 ሽጉጦች፣ 924 የተለያዩ ጠመንጃዎች በአጠቃላይ 2 ሺህ 772 የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያዎች ከ80 ሺህ 241 ልዩ ልዩ ጥይቶች ጋር ተይዘዋል ብሏል፡፡
እንዲሁም 1 ሺህ 312 የተለያዩ የፀጥታ አካላት የደንብ አልባሳት እና በርካታ የተለያዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶች በፍተሻው ወቅት መገኘታቸውንም ገልጿል፡፡
በተጨማሪም 1 ሺህ 799 አዳዲስ ሲም ካርዶች፣ 6 የውጭ ሃገር ስልክ መጥለፊያ መሳሪዎች ፣ 629 ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ ልዩ ልዩ የባንክ የሂሳብ ደብተሮች እና ማህተሞች እንዲሁም በፀጥታ ሃይሎች እጅ ብቻ ሊገኙ የሚገባቸው በርካታ ቁሳቁሶች መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የፀጥታ አካላት እና የከተማዋ ነዋሪዎች በመቀናጀት እየሰሩት ባለው ስራ ሁከት እና ሽብር መፍጠር የሚያስችል ክፍተት ማግኘት ያልቻሉት የጁንታው ተላላኪዎች ለጥፋት ተግባር ያዘጋጇቸውን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በሰው ላይ ጉዳት ለማድረስ እና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ በተለያዩ ቦታዎች እየጣሉ እንደሚገኙ ያስታወሰው ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደትም 25 የእጅ ቦምብ፣ 4 ልዩ ልዩ ፈንጂዎች፣ 11 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ 40 ሽጉጥ፣ 6 የተለያዩ ጠመንጃዎች ከመሰል 914 ጥይቶቻቸው ጋር ተጥለው በህብረተሰቡ ጥቆማ ከተጣሉበት ስፍራ በፀጥታ አካላት መነሳታቸውንም ነው የገለጸው፡፡
የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ እየተከናወነ ባለው ህግ የማስከበር እንቅስቃሴ ወቅት በፍተሻ እና በብርበራ ከተያዙት የጦር መሳሪያዎች ባሻገር ከ4 ሚሊየን 300 ሺህ በላይ ብር ፣ 248 ሺህ 941 የአሜሪካ ዶላር፣ 3 ሺህ 172 ዩሮ እና ከ192 ሺህ በላይ የተለያዩ ሃገራት ገንዘቦች መያዛቸውንም ኮሚሽኑ አመልክቷል፡፡
ባለፈው አንድ ወር ውስጥ በከሃዲው የህወሓት ጁንታ ቡድን እና ተላላኪዎቹ ላይ እየተወሰደ ካለው ህግን የማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተጠረጠሩ 1 ሺህ 127 ግለሰቦች መካከል 1 ሺህ 88ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና በ1 ሺህ 938 የክስ መዝገብ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም አስረድቷል፡፡
ለፀጥታ ስጋት ይሆናሉ ተብለው በተጠረጠሩ መኖሪያ ቤቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ የሚያደርገውን ብርበራ እና ፍተሻ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፀው ኮሚሽኑ ህብረተሰቡ ድጋፍና ጥቆማ በመስጠት እንደ እስካሁኑ ከፖሊስ ጎን እንዲቆም ጠይቋል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.