Fana: At a Speed of Life!

ኮሎኔል ፍስሃ በየነን ጨምሮ አምስት የመከላከያ መኮንኖች በነበሩ ግለሰቦች ላይ ለመርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ 13 ቀናት ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ኮሎኔል ፍስሃ በየነን ጨምሮ አምስት የመከላከያ መኮንኖች በነበሩ ግለሰቦች ላይ ለተጀመረው ምርመራ ተጨማሪ 13 ቀናት ተፈቀደ።

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው የታዩት ተጠርጣሪዎች፤ በእነ ኮሎኔል ፍስሃ በየነ መዝገብ የተከሰሱት እነ ኮሎኔል ሃይላይ መዝገቡ፣ ሌተናል ኮሎኔል ሙዘይ ተሰሜ፣ ኮሎኔል ሰመረ በርሄ እና ሌተናል ኮሎኔል ባራኪ ጡማሎው ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹ የህወሓትና የጸረሰላም ቡድኖችን ተልዕኮ በመቀበል ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ ሲቀሳቀሱ ነበር ተብለው የተጠረጠሩ መሆናቸው ተገልጿል።

መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው የምርመራ ጊዜ የሰራውን ስራ ይፋ አድርጓል።

በዚህም በአዲስ አበባ ተልዕኮ ተቀብለው በመደራጀት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር እንዲሁም በሰሜን እዝ ጦር ላይ ጥቃት እንዲፈጸም በህቡዕ ኔትዎርክ በማቋረጥ ሲሰሩ እንደነበር በመረጃ አረጋግጫለሁ ብሏል ለችሎቱ።

ተጠርጣሪዎቹ ከኦነግ ሸኔ አመራሮች ጋር በመገናኘት ለጸረ ሰላም ሃይሎች በመንግስት በጀት ስልጠና ሲሰጡ እንደነበር ባገኘሁት ማስረጃ አረጋግጫለሁ ያለው ፖሊስ፤ በመኖሪያ ቤታቸው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ባደረኩት ብርበራ በበርካታ ባንኮች የተከፈቱ በርካታ ገንዘብ የተዘዋወረበት ደብተሮች ማግኘቱን በመጥቀስ በዚህ ላይ ለማን እና መቼ ተዘዋወረ የሚለውን ጉዳይ እያጣራሁ ነው ብሏል።

ቀሩኝ ባላቸው ስራዎቹም ከተለያዩ ባንኮች የገንዘብ ዝውውሩን በሚመለከት መረጃ ለማሰባሰብ፣ያልተያዙ ግብረ-አበሮቻቸውን በክትትል ለመያዝ ፤ የተለዋወጡትን የስልክ ልውውጥ በማስረጃ ለመለየትና ቀሪ ምርመራዎችን ለማከናወን ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል።

1ኛ ተጠርጣሪ ኮሎኔል ፍስሃ በየነ እኔ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት የለኝም መርማሪ ፖሊስን በቀጣይ አዙሬ እዚሁ አቆመዋለሁ በማለት ሲዝቱ ተደምጠዋል።

የቤተሰብ ቀለብ በመታገዱ ልጆቼ ተቸግረዋል ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ይስጥልኝ ሲሉም አቤቱታ አቅርበዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ 1ኛ ተጠረጣሪው ኮሎኔል ፍስሃ ህገ -መንግስቱን በሃይል ለመናድ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር መጠርጠራቸውን ተከትሎ አሁንም እየተናገሩ እና እያስፈራሩኝ ያሉት በሃይል ህገ-መንግስቱን ገልብጬ እዚህ አቆምሃለው ነው እያሉ እየዛቱበኝ ነው በማለት ፍርድ ቤቱ ይህን ዛቻ ይመዝግብልኝ ሲል አስገንዝቧል።

ሌሎቹ ተጠርጣሪዎችም የቀረበው የጅምላ ክስ ነው፤ በተናጠል ተሳትፏችን ሊገለጽ ይፈገባል ሲሉ መቃወሚያ አሰምተዋል።

የባንክ አካውንታቸው እንዳይንቀሳቀስ በመደረጉ ቤተሰቦቻቸው ለችግር እየተዳረጉ መሆኑን፣ ጠበቃ ለመቅጠር አቅም እንደሌላቸውና መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡትን የባንክ አካውንት የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ለምን እንዳልተለቀቀላቸው እንዲያስረዳ እና ጠበቃ ለማቆም አቅም የለንም ሲሉ የመንግስት ጠበቃ እንዲቆምላቸው 1ኛ ተጠርጣሪ ኮሎኔል ፍስሃ በየነ እና 5ኛ ተጠርጣሪ ሌተናል ኮሎኔል ባራኪ ጡማሎው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

የጡረታ ባንክ ደብተራችን ታግዷል ያሉት ተጠርጣሪዎቹ የጡረታ ደብተራቸው እንዲመለስላቸው በማዘዝ ለመርማሪ ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ የ13ቱን ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.